Wednesday, May 21, 2014

የሰላት ወቅቶች። የዙህር ወቅት፣ የዐስር ሰላት ወቅት


የሰላት ወቅቶች

ግዴታ የሆኑ ሰላቶች በሀያ አራት ሰዐት ውስጥ አምስት ሲሆኑ ለእያንዳንዱ ሰላት የተወሰኑ ወቅቶች አሏቸው፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል፡-
‹‹ሶላት በምእምናን ላይ በጊዜያት የተወሰነች ግዴታ ናትና፡፡›› (አል ኒሳእ:1ዐ3)
በመሆኑም ወቅቱ ሳይደርስ የሚሰገድ ሰላት ተቀባየይነት የለውም፡፡ 
ስለ ሰላት ወቅት ከሚጠቅሱ ሀዲሶች ዋናው ኢብኑ ዑመር ያስተላለፉት ሀዲስ ሲሆን
ነብዩ (ﷺ)እንዲህ እንዳሉ አስተላልፈውልናል :-

“የዙህር ወቅት ፀሐይ ወደ ምዕራብ ዘንበል ካለችበት ሰዓት ጀምሮ የአንድ ሰው ጥላ ከቁመቱ እኩል ሊሆን ትንሽ እስኪቀረው ድረስ ነው፡፡ 
የዓስር ወቅት ደግሞ የፀሐይ ጥላ ከአንድ ሰው ቁመት እኩል ከሚሆንበት ሰዓት ጀምሮ ፀሐይ ደብዘዝ እስክትል:: 
የመግሪብ ወቅት ፀሐይ ከጠለቀችበት ሰዓት ጀምሮ የሰማይ ደንገዝገዝ እስኪሰወር:: 
የዒሻ ወቅት ደግሞ እስከ እኩለ ለሊት ድረስ ሲሆን 
የሱብሂ ሰላት ወቅት ደግሞ ጐህ ከቀደደ ጀምሮ ፀሐይ ልትወጣ ትንሽ እስከሚቀራት ድረስ ነው፡፡”(ሙስሊም ዘግበውታል)

የዙህር ወቅት
የዙህር ወቅት ፀሐይ ከእኩለ ሰማይ ወደ ምዕራብ ዘንበል ስትል ጀምሮ የአንድ ነገር ጥላ ከርዝመቱ እኩል እስከሚሆን ድረስ ሲሆን በመጀመሪያው ወቅት ላይ መስገድ ግን የተወደደ ነው፡፡ ነገር ግን ጠራራ ፀሐይ ከሆነ ትንሽ በረድ እስከሚል ድረስ ማዘግየት የበለጠ ይወደዳል፡፡ ነብዩ እንዲህ ብለዋል 
“ሙቀት ከፍተኛ ሲሆን ትንሽ በረድ አድርጋችሁ ዙህርን ስገዱ ከፍተኛ ሙቀት የጀሀነም እንፋሎት ነው፡፡”(ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

የዐስር ሰላት ወቅት
የዐስር ሰላት ወቅት የአንድ ነገር ጥላ ከቁመቱ እኩል ከሆነበት ማለትም ከዙህር ማብቂያ ወቅት ጀምሮ ፀሐይ ሊጠልቅ ትንሽ እስከሚቀረው ድረስ ሲሆን ዐስርንም በመጀመሪያው ወቅት መስገድ ሱና ነው፡፡ እንዲያውም መካከለኛይቱ ሰላት በማለት አላህ እንዲህ ሲል የገለፀው ነው፡-
‹‹በሶላቶች (በተለይ) በመካከለኛይቱም ሶላት ላይ ተጠባበቁ፡፡ ታዛዦች ኾናችሁም ለአላህ ቁሙ፡፡›› (አል በቀራህ 238)
ነብዩም (ﷺ) እንድንከባከበው እንዲህ በማለት አዘዋል 
“የዐስር ሰላት ያመለጠው ቤተሰቦቹንና ንብረቱን እንዳጣ ነው፡፡”(ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል) 
በሌላም ሀዲስ እንዲህ ብለዋል
“የዐስር ሰላትን የተወ ሰው ስራው ይታበስበታል፡፡”( ቡኻሪ ዘግበውታል)

የዕለቱ ጥያቄ ይሳተፉ
የዓስር ወቅት መቼ ነው?




ከ www.facebook.com/easyfiqh የተወሰደ።

No comments:

Post a Comment