Wednesday, July 30, 2014

ሴት ልጅ ካለዎት ታድለዋል!


ሴት ልጅ ካለዎት ታድለዋል! 
በአላህ ስም እጅግ በጣም አዛኝ እና ሩህሩህ በሆነው እጀምራለሁ
የአላህ መልእክተኛ صلى الله عليه وسلم እንዲህ ብለዋል፤
«من ابتلى من هذه البنات بشيء, فأحسن إليهن كن له ستراً من النار» رواه البخاري (5995) ومسلم (2629) وفي لفظ له: (من ابتلى بشيء من البنات فصبر عليهن كن له حجاباً من النار) رواه الترمذي (1913) وصححه الألباني رحمه الله.
(ከእናንተ መካከል ከሴት ልጆቹ ፈተና የገጠመውና፣ ለእነርሱም መልካምን የዋለ ከእሳት ከለላ ይሆኑለታል።)
ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል
ሴት ልጆችን ማሳደግ ከባድ ደረጃ እንዳለው በመግለፅና ልዩ እንክብካቤ እንዲደረግላቸው በማበረታታት
ነው ይህንን ያሉት።
አል አይኒ የተባሉት የሀዲስ ተንታኝ (ኡምደቱል ቃሪ) በተሰኘው ኪታባቸው እንዲህ ብለዋል፤
«እነዚህ ሀዲሶች፤ ከወንድ ልጆች ይልቅ ሴት ልጆች ያላቸውን ሀቅ ያስረግጣሉ፤ ይህም ሴቶች፤ ተሯሩጠው እራሳቸውን ከመቻል አንፃር ደከም ስለሚሉ ነው»
ሴት ልጅሽ የወደፊት እናት ነች።
እናት ደግሞ የልጆች የመጀመሪያ ትምህርት ቤት ነች። ሴት ልጆቻችንን በተለየ ትኩረት ኢስላማዊም ይሁን ዱንያዊ ትምህርቶችን ሸሪአን በጠበቀ መልኩ ማስተማር አለብን።
ሴት ልጅን ማስተማር ማህበረሰብን ማስተማር ነው። በመልካም ሴት ታንፀው የሚያድጉ ልጆች ለወደፊቱ ማህበረሰብ የጀርባ አጥንት ናቸውና ሴቶችን በማስተማር
ሃላፊነት የሚሰማው ትውልድ እንዲፈጠር አስተዋፅኦ እናበርክት።
ሴት ልጅ ከተማረች መብትና ግዴታዋን ስለምታውቅ፤ የባልዋን፣ የወላጆችዋን፣ የልጆችዋን፣ የዘመዶችዋንና፣ የጎረቤቶቿን ሃቅ አላህን በሚያስደስት መልኩ ትጠብቃለች።
የራሷንም መብትና ግዴታ ስለምታውቅ ለበደል አትጋለጥም።
ስለዚህ ለራስዎ፣ለቤተሰብዎ እንዲሁም ለማህበረሰቡ ሲሉ ከጎኗ በመሆን በማረም፣ በማበረታታት፣ በማስተማር እና በመርዳት ሊያግዟት ይገባል።
ውድ ወላጅ!
ልጅዎትን ዲንን በማሳወቅ የተጣለብዎትን ከባድ ሃላፊነት ለመወጣት ከአላህ ከባድ ምንዳ ለማግኘት አሁኑኑ ይንቀሳቀሳሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
አላህ ብርታቱን ይስጠዎት!!

#ሊንኩን_በመጫን_ፔጁን_ላይክ(like) _ያድርጉ =====>
--------------------------------
www.facebook.com/tenbihat--------------------------------
ኢንሻ አላህ ጠቃሚ ኢስላማዊ ዕውቀትን ይገበዩበታል!!!
ሼር ማድረግ እንዳይረሱ!

Friday, July 25, 2014

ከረመዳን የመጨረሻዎቹ አስርት ቀናት




ከረመዳን የመጨረሻዎቹ አስርት ቀናት
በጣሀ አህመድ የተዘጋጀ
✔ የረመዳን ወር ታላቅ ወር መሆኑ ለሁላችንም ግልጽ ነው፡፡ ስለታላቅነቱም ብዙ ሳንሰማ ወይም ሳናነብ አልቀረን ይሆናል፡፡ የረመዳን ወር የላቀ ታላቅ ወር እንደመሆኑ ሁሉ ከቀናቶቹና ከለሊቶቹ የመጨረሻዎቹ አስሩ ለየት ያለ ቦታ ሊሰጣቸው የሚገቡ ናቸው፡፡ እነዚህን አሰርት የረመዳን የመጨረሻ ቀናት በተለይም ለሊቶቻቸውን ታላቅ ደረጃ ልንሰጠቸው እንደሚገባ የሚያመለክቱ የተወሰኑ ነጥቦችን በአጭሩ ለመጥቀስ እወዳለሁ፤
✔ አንደኛ፡- የአላህ መልዕክተኛ በነዚህ አስርት ቀናት እና ለሊቶች የነበራቸው የአምልኮ ሁኔታ የምዕመናን እናት ዓኢሻ (ረዲየላዑ ዓንሀ) እንዲህ ብለዋል፡፡ ‹‹የአላህ መልዕክተኛ ከረመዳን የመጨረሻዎቹ አስርት ከሌላ ጊዜ በተለየ መልኩ (በዒባዳ) ላይ ይተጉ ነበር›› ሙስሊም ዘግበውታል
የአላህ መልዕክተኛው የለሊቱ አብዛኛውን ክፍል ከእንቅልፍ በመራቅ ህያው ያደርጉት ነበር፡፡
ዓኢሻ (ረዲየላዑ ዓንሀ) እንዲህ ብለዋል፡፡ ‹‹ የአላህ መልዕክተኛ ከረመዳን የመጨረሻዎቹ አሰርት ቀናት ሲገባ ለሊቱን በዒባዳ ላይ በማሳለፍ ህያው ያደርጉ፣ ቤተሰባቸውን ያነቃቁ (ይቀሰቅሱ) ፣ ቀበቷቸውን በማጥበቅ ይተጉ ነበር፡፡›› ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል
በሐዲሱ ውሰጥ ‹‹ቀበቷቸውን ያጠብቁ ነበር›› በሚል የተጠቀሰውን ቃል በተመለከተ ብዙ የሐዲስ ተንታኞች እንዳሉት ‘‘አሽሙራዊ አገላለፅ ሲሆን ለማለት የተፈለገውም በከፍተኛ ሁኔታ በዒባዳ ከመጠመዳቸው በመነሳት ከሴቶቻቸው ይርቁ ነበር ለማለት ነው’’ ፡፡

✔ ሁለተኛ፡- የእነዚህን አሰርት ቀናት እና ለሊቶች ታላቅነት የሚያሳየን በውስጣቸው ‹‹ለይለተል ቀድር›› የተባለችው ለሊት መኖር ነው፡፡ ይህች ለሊት ከሌሎች የምትለይበት ብዙ መለያዎች ያላት ስትሆን ከነርሱም መካከል፡-
1. ቁርአን የወረደባት ለሊት መሆኗ 
2. ከአንደ ሺህ ወራት የምትበልጥ መሆኗ 3. የተባረከች መሆኗ 
4. ጅብሪል በመልዕክት በብዛት የሚወርዱባት መሆኗ 5. ብዙ ሰዎች በከፍተኛ አምልኮ ውሰጥ የሚገቡ ከመሆኑ አንፃር ከእሳት ነፃ የሚወጡባት ለሊት መሆኗ 
6. በዚህች ለሊት አላህ ምንዳውን እንደሚከፍለው በእርግጠኝነት በማመን እንዲሁም ከይዩልኝ እና መሰል ዱንያዊ ፍላጐቶች ርቆ ሰላትን መስገድ ያበዛ ወንጀሉ የሚታበስ መሆኑ ነው፡፡

✔ ሶስተኛው፡- በእነዚህ አስር ቀናት ኢዕቲካፍ መግባት የመልዕክተኛው ሱና ነው፡፡ ኢዕቲካፍ ማለት እራስን ለአምልኮ ብቻ በመወሰን በመስጂድ መዘውተር ነው፡፡
እናታችን ዓኢሻ እንዲህ ብለዋል፤ ‹‹ነብዩ እስኪሞቱ ድረስ ከረመዳን የመጨረሻዎቹን አስርት ቀናት እራሳቸውን ለአምልኮ ብቻ በመወሰን በመስጂድ ይዘወትሩ ነበር፡፡›› ቡኻሪ እና ሙስሊም ዘግበውተል
⇔ ከዚህ በመቀጠል ከኢዕቲካፍ ጋር ተያያዥነት ያለውን ይህንን ፈትዋ ወይም ጥያቄና መልስ እንመለከታለን፡፡
☞ ጥያቄ፡- የኢዕቲካፍ መስፈርቶች የትኞቹ ናቸው? 
ፆም ከመስፈርቶቹ ይካተታልን? አንድ ሰው በኢዕቲካፍ ላይ እያለ በሽተኛን መጠየቅ፣ በግብዣ ቦታ ላይ መገኘት፣ የቤተሰቦቹን ጉዳይ ማስፈፀም፣ አስክሬን መሸኘት ወይም ወደ ስራው መሄድ ይችላልን?

☞ መልስ፡- ሰላተል ጀመዓ በሚሰገድባቸው መስጂዶች ሁሉ ኢዕቲካፍ ማድረግ የተደነገገ ነው፡፡ ነገር ግን ኢዕቲካፍ የሚያደርገው ሠዉ ሰላተል ጁምዓ ግዴታ ከሚሆንባቸው ሰዎች መካከል ከሆነና ከኢዕቲካፍ ቀናት መካከል የጁምዓ ቀን ካለ ሰላተልጁምዓ በሚሰገድበት መስጅድ ውስጥ ኢዕቲካፍን ማድረጉ የተሻለ (በላጭ) ነው፡፡
ፆም የኢዕቲካፍ መስፈርት አይደለም፡፡ 
በኢዕቲካፍ ላይ ያለ ሰው በዚያ ወቅት በሽተኛን አለመጠየቁ፣ ጥሪ ቢቀርብለት በጥሪ ቦታ ላይ አለመገኘቱ፣ የቤተሰቦቹን ጉዳዬች አለማስፈፀሙ፣ አስክሬን አለመሸኘቱ፣ ከመስጂድ ውጪ ወደ ስራው አለመሄዱ ሱና ነው፡፡ ይህም እናታች ዓኢሻ በትክክለኛ ሰነድ እንዲህ ማለታቸው የተረጋገጠ በመሆኑ ነው፡፡ ‹‹በኢዕቲካፍ ላይ ያለ ሰው በሽተኛን አለመጠየቁ፣ የአስክሬን አሸኛኘት ላይ አለመገኘቱ፣ ግንኙነትን አለመፈፀሙም፣ በስሜት ከተቃራኒ ፆታ ጋር አለመነካካቱ፣ አስገዳጅ ለሆነ ጉዳይ ቢሆን እንጂ ከኢዕቲካፍ አለመውጣቱ ሱና ነው፡፡›› አቡዳውድ እና ዳረቁጥኒ ዘግበውታል

ቋሚ የፈትዋ ኮሚቴ 
አብዱላህ ቢን ቁዑድ 
አብዱረዛቅ ዓፊፊ 
አብዱል ዓዚዝ ኢብን ባዝ

Friday, July 18, 2014

ዘካ



ዘካ:- የስርወ-ቃሉ ቋንቋዊ ትርጉም፦ "መብዛት"፣ "ማደግ"፣ "መጨመር" እንዲሁም "ማወደስ"ና "(ከጉድፈት) ማጥራት"ን የሚያመለክት ነው። 

የዘካ ሸሪዓዊ መልእክት ደግሞ፦ በየተወሰኑ ጊዜያት ከተወሰኑ የንብረት ዓይነቶች ተቆንጥሮ ለተወሰኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች በግዴታነት የሚሰጥ የተገደበ ወጪ ነው። 

የዘካህ ድንጋጌ እንደሌሎቹ መለኮታዊ ህግጋት ሁሉ ከአምልኮ ዘርፍነቱ ባሻገር ድንቅ፣ ብርቅና ፅድቅ ጥበቦችንና ዓላማዎችን ያነገበ ነው። 

ሰዎች ሊረዷቸው ከሚችሏቸው ግለሰባዊና ማሕበራዊ ጥቅሞቹና የመፍትሄነት ገፅታዎቹ መካከል፦ 

1. ለችግረኞች መረጃ መሆኑ፣ 
2. ለድሆች መቋቋሚያ መሆኑ፣ 
3. በእምነት ላይ የተመሠረተ የወዳጅነትና የወንድማማችነት ትስስርን ማጥበቁ፣ 
4. ስብዕናን ከስስትና ከንፉግነት ማፅዳቱ፣ 
5. ድሆች ለሀብታሞች ያላቸውን ምልከታ ከምቀኝነት ማጥራቱ 
6. በድህነት ምክንያት የሚፈጸሙ ወንጀሎችን መገደቡ 
7. ከገንዘብ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጥቅል ኢስላማዊ ጉዳዮችን 
8. ለማቀላጠፍ ምክንያት መሆኑና፣ 
9. የንብረት በረከት ማስከተሉ ጥቂቶቹ ናቸው። 

በኢልያስ አህመድ ከተዘጋጀው “የዘካ ህግጋት አጭር ማብራርያ” የተወሰደ

Tuesday, July 8, 2014

የረመዷን ወር ተከታታይ ትምህርት



የረመዷን ወር ተከታታይ ትምህርት 

አቡ ሁረይራ (ረድየላሁ ዓንሁ) በዘገቡት ሐዲስ ረሱል (ሰለላሁ ዓለይህ ወሰለም)<<የረመዷን ወር ሲገባ የሰማይ በሮች ይከፈታሉ የጀሀነም በሮች ይዘጋሉ ሸይጧኖችም ይታሰራሉ>> ብለዋል
ቡኻሪ ሙስሊም ዘግበውታል