Tuesday, June 3, 2014

የሰላት ወቅቶች። የመግሪብ ሰላት ወቅት ፣ የሱብሂ ሰላት ወቅት





የመግሪብ ሰላት ወቅት

የመግሪብ ሰላት ወቅት ፀሐይ ከጠለቀበት ሰዓት ጀምሮ ደንገዝ እስከሚል (ፀሀይ መጥለቂያ ጋር የሚኖረው የሰማይ ቅላት እስከሚሰወር) ሲሆን መግሪብንም በመጀመሪያው ወቅት ላይ መስገድ ሱና ነው፡፡ ነብዩ (ﷺ) እንዲህ ብለዋል 
“ህዝቦቼ መግሪብን ከዋክብት እስኪጠላለፉ ድረስ ካላዘገዩ በመልካም ላይ ናቸው፡፡” (አህመድ አቡዳውድና ሃኪም ዘግበውታል)
የሐጅ ተግባር ላይ ያለ ሰው ግን የሙዝደሊፋን ሌሊት መግሪብን ወደ ዒሻ አዘግይቶ ከዒሻ ጋር መስገዱ የተወደደ ተግባር ነው፡፡
የዒሻ ሰላት ወቅት

የዒሻ ሰላት ወቅት ደግሞ እስከ እኩለ ለሊት የሚቆይ ሲሆን ዒሻን ግን አስቸጋሪ ካልሆነ አዘግይቶ በመጨረሻው ወቅት መስገድ ይበልጥ የተወደደ ነው፡፡ ከዒሻ በፊት መተኛትና ከዒሻ በኋላ ደግሞ ወሬ ማውራት የተጠላ ነው::
አቡ በርዛህ ባስተላለፉት ሀዲስ 
“ነብዩ ከዒሻ በፊት መተኛትና ከዒሻ በኃላ ማውራት ይጠሉ ነበር::”(ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

የሱብሂ ሰላት ወቅት

የሱብሂ ሰላት ወቅት ደግሞ ጐህ ከቀደደ ጀምሮ ፀሐይ እስክትወጣ ድረስ ሲሆን የጐህ መቅደድ እንደተረጋገጠ ወዲያው መስገድ የተወደደ ነው፡፡
እነዚህ ለሰላት የተደነገጉ ወቅቶች በመሆናቸው ማንኛውም ሙስሊም የሰላት ወቅቶችን እየተጠባበቀ ሳያዘገይ በተወሰነላቸው ወቅቶች ሊሰግድ ይገባል፡፡ አላህ ሰላትን የሚያዘገዩን ሰዎች እንዲህ በማለት ዝቶባቸዋል፡-
‹‹ወዮላቸው ለሰጋጆች፡፡ ለእነዚያ እነርሱ ከስግደታቸው ዘንጊዎች ለኾኑት፤ (ሰጋጆች)፡፡›› (አል ማዑን 4-5)
በሌላ አንቀፅም እንዲህ ብሏል፦
‹‹ከእነሱም በኋላ ሶላትን ያጓደሉ (የተዉ) ፍላጎቶችንም የተከተሉ መጥፎ ምትኮች ተተኩ! የገሀነምንም ሸለቆ በእርግጥ ያገኛሉ፡፡›› (መርየም 59)
ሰላቶችን በወቅቶቻቸው መስገድ አላህ ዘንድ በጣም ከሚወደዱና ብልጫ ካላቸው ስራዎች የሚመደብ ነው፡፡ ነብዩ (ﷺ) አላህ ዘንድ በጣም የሚወደድን ስራ ሲጠየቁ 
“ሰላቶችን በወቅቶቻቸው መስገድ” በማለት መልሰዋል:: (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

የዕለቱ ጥያቄ ይሳተፉ
ነብዩ (ﷺ) አላህ ዘንድ በጣም የሚወደድን ስራ ሲጠየቁ የመለሱት ምን በማለት ነው?

ከ www.facebook.com/easyfiqh የተወሰደ።


No comments:

Post a Comment