Thursday, December 24, 2015

ያስፈልገዎታል!! ጀናባን የሚመለከቱ ህግና ደንቦች።

ከወንድም ኢብኑ ሙነወር የተወሰደ።

ያስፈልገዎታል!!
                         ጀናባን የሚመለከቱ ህግና ደንቦች

የቃላት መፍቻ፡-

1.   መኒይ (የዘር ፈሳሽ)፡-

- በስሜት ተስፈንጥሮ ከእርካታ ጋር የሚወጣ ፈሳሽ ነው፡፡
- ለወንድ ወፍራምና (ወደ ቢጫነት የሚያደላ) ነጭ ፈሳሽ ሲሆን ለሴት ደግሞ ቀጭንና ቢጫ ነው፡፡ [ሙስሊም፡ 311] ሽታው ወደሊጥ ሽታ የቀረበ ነው፡፡ በሆነ ምክንያት እነዚህ መታወቂያዎች ሊቀየሩ ይችላሉ፡፡
- ከወጣ በኋላ የሰውነት መቀዝቀዝ ዘና ማለት (ፉቱር) ይከተላል፡፡
- ፈሳሹ ሚዛን በሚደፋው የዑለማእ እይታ ጦሀራ እንጂ ነጃሳ አይደለም፡፡ ይህን የሚደግፉ ሶሒሕ ማስረጃዎች መጥተዋል፡፡ [ሙስሊም፡ 694] [አልኢርዋእ፡ 1/197]
- በውንም ይሁን በህልም ከወጣ ገላን መታጠብ ግዴታ ነው፡፡

2.   መዚይ፡-

- ግንኙነትን ሲታሰብ ወይም ሲፈለግ የሚወጣ ያዝ የሚያደርግ (የሚያጣብቅ)፣ ቀለም አልባ ቀጭን ፈሳሽ ነው፡፡
- አወጣጡ ከእርካታ ጋር አይደለም፡፡ ተስፈንጥሮ ስለማይወጣ መውጣቱ ላይስተዋል ይችላል፡፡
- ነጃሳ ስለሆነ የነካውን አካል ማጠብ ይገባል፡፡ ልብስን ግን የነካው ቦታ ላይ ውሃ በመርጨት ማፅዳት በቂ ነው፡፡
- የነካውን ቦታ እንጂ ገላን መታጠብ ግን ግዴታ አይደለም፡፡ ውዱእን ግን ያፈርሳል፡፡

3.   ወዲይ፡-

- ከሽንት በኋላ የሚወጣ ነጭ ሽታ አልባ ፈሳሽ ነው፡፡
- የሚያጣብቅ አይደለም፡፡
- ብይኑ ከሽንት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

4.   ከሴቶች ብልት የሚወጣ ፈሳሽ፡-

- ከማህፀን የሚወጣ ቀጭን ፈሳሽ ነው፡፡ መጠኑ ከሴት ሴት ይለያያል፡፡
- ሴቷ መውጣቱንም ላታስተውለው ትችላለች፡፡
- አካልንም ልብስንም ቢነካ አይነጅስም፣ ጦሃራ ነው፡፡
- ውዱእን ግን ያፈርሳል፡፡ ከሁለቱም መፀዳጃዎች በኩል የሚወጣ ነገር ውዱእ ያፈርሳልና፡፡ አወጣጡ ቋሚ ከሆነ ግን ለያንዳንዱ ሶላት ወቅቱ ከገባ በኋላ ውዱእ እያደረገች መስገድ ይገባል፡፡ ውዱእ ካደረገች በኋላ ቢወጣ ቦታም አይሰጠውም፡፡

                      ገላን መታጠብ ግዴታ የሚሆነው መቼ ነው?

1. በውኑ ግንኙነት ከተፈፀመ የዘር ፈሳሽ (መኒይ) #ቢፈስም_ባይፈስም ትጥበት ግዴታ ነው፡፡
2. ግንኙነት #ባይፈፀምም የዘር ፈሳሽ (መኒይ) #ከእርካታ ጋር ከወጣ ትጥበት ግዴታ ነው፡፡
3. በህልሙ ግንኙነት እንደፈፀመ አይቶ የዘር ፈሳሽ (መኒይ) ካገኘ በማያሻማ መልኩ መታጠብ ግዴታ ነው፡፡
4. በህልሙ ግንኙነት እንደፈፀመ አይቶ ነገር ግን ሲነቃ ምንም አይነት የዘር ፈሳሽ (መኒይ) ካላገኘ በማያሻማ መልኩ የመታጠብ ግዴታ የለበትም፡፡ ኡሙ ሱለይም የተባለችዋ ሶሐቢያህ ረዲየላሁ ዐንሃ “የአላህ መልእክተኛ ሆይ! አንዲት ሴት ኢሕቲላም ከሆነች (በህልሟ ግንኙነት ስትፈፅም ካየች) የመታጠብ ግዴታ አለባትን?” ብላ ስትጠይቅ “ፈሳሽ ካየች አዎ” ሲሉ መልሰውላታል፡፡ [ቡኻሪና ሙስሊም]
5. በህልሙ ግንኙነት ሲፈፅም አላየም ወይም አያስታውስም፡፡ ነገር ግን ሲነቃ የዘር ፈሳሽ (መኒይ) ካገኘ በማያሻማ መልኩ የመታጠብ ግዴታ አለበት፡፡
6. በህልሙ ግንኙነት ሲፈፅም አላየም ወይም አያስታውስም፡፡ ነገር ግን ሲነቃ ፈሳሽ አገኘ፡፡ የዘር ፈሳሽ (መኒይ) እንዳልሆነ እርግጠኛ ከሆነ የመታጠብ ግዴታ የለበትም፡፡ የነካውን ግን ሊያጥብ ይገባል፡፡ ብይኑ የሽንት ብይን ነውና፡፡
7. በህልሙ ግንኙነት ሲፈፅም አላየም ወይም አያስታውስም፡፡ ነገር ግን ሲነቃ የዘር ፈሳሽ (መኒይ) ይሁን አይሁን #መለየት_ያልቻለው ፈሳሽ ካገኘ በ ሽታ ወይም በቻለው መንገድ ለመለየት ይሞክርና ጥርጣሬው መኒይ ወደመሆኑ ካደላ ይታጠብ፡፡ ጥርጣሬው መዚይ ወደመሆኑ ካደላ ግን በተለይም ከመተኛቱ በፊት ስለ ግንኙነት አስቦ ከነበር እንደ መዚይ ይቁጠረውና የነካውን ቦታ ብቻ ይጠብ፡፡ ገላውን የመታጠብ ግዴታ የለበትም፡፡ ቢታጠብ ከጥንቃቄ አንፃር የተሻለ ነው፡፡
8. በህልሙ ግንኙነት ሲፈፅም አላየም ወይም አያስታውስም፡፡ ነገር ግን ሲነቃ የዘር ፈሳሽ (መኒይ) ይሁን አይሁን #መለየት_ያልቻለው ፈሳሽ ካገኘና ግምቱ ወደየትኛውም ካላደላ፣ ከመተኛቱ በፊት ስለ ግንኙነት #ያላሰበ ከሆነ ጉዳዩ አወዛጋቢ ቢሆንም ትክክለኛው ትጥበት የለበትም የሚል ነው፡፡ ቢታጠብ ከጥንቃቄ አንፃር የተሻለ ነው፡፡ [ፈታዋ ኢብኑልዑሠይሚን፡ 11/161]

የጀናባ አስተጣጠብ ሁለት አይነት ነው፡፡

1. የሚያብቃቃ ማለትም ግዴታውን ለማውረድ የሚጠበቅ ሲሆን እሱም ሙሉ አካልን በውሃ ማዳረስ ነው፡፡ ባይሆን መጉመጥመጥና በአፍንጫ ውሃ መሳብ (ኢስቲንሻቅ) እንዳይረስ፡፡ ለትጥበት ኒያ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ አንድ ሰው ጀናባ ማውረድን ሳያስብ እንዲሁ ውሃ ውስጥ ዋኝቶ ቢወጣ መላ አካላቱ ውሃ መንካቱ ብቻ ጀናባው ለመውረዱ በቂ አይሆንም፡፡ ይስተዋል! ይህን ትጥበት ካደረጉ በኋላ ውዱእም ባያደርጉ መስገድ ይቻላል፡፡ ባይሆን ከትጥበቱ መሀል ውዱእ የሚያፈርስ ነገር መፈፀም የለበትም፡፡
2. ሌላኛውና በላጩ ግን በቅድሚያ ሁለት እጆችን መታጠብ፡፡ ከዚያም ኢስቲንጃእ ማድረግ፡፡ ከዚያም ውዱእ ማድረግ፡፡ ከዚያም ከእራስ ጀምሮ ቀሪ አካላትን ውሃ ማዳረስ፡፡ እግርን ከውዱእ ጋር ማጠብም ይቻላል፤ መጨረሻ ላይ ማጠብም ይቻላል፡፡ [ቡኻሪና ሙስሊም]

ማሳሰቢያ፡-

ሴቷ ለትጥበት ስትል የፀጉር ጉንጉኗን የመፍታት ግዴታ የለባትም፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም: ኡሙ ሰለማህ ለጀናባህ ወይም ለሐይድ ትጥበት ፀጉሯን “ልፍታው ወይ?” ብላ ስትጠይቃቸው “አይ! የሚበቃሽ ከእራስሽ ላይ ሶስት ጊዜ ውሃ ማፍሰስ ብቻ ነው” ብለዋታል፡፡ [ሙስሊም] ስለዚህ ፀጉር ሳይፈታ ውሃ መድረስ ከቻለ መፍታት አይጠበቅም፡፡

ለማጣቀሻነት የተጠቀምኩት
1. ፈታዋ ኢብኑልዑሠይሚን
2. ፈትሑልዐላም ፊ ዲራሰቲ አሓዲሢ ቡሉጊልመራም እና ሌሎችም
ሼር ማድረግ እንዳይረሱ፡፡

(ኢብኑ ሙነወር፣ ህዳር 8/2008)

Friday, November 27, 2015

ኔትዎርክ ማርኬቲንግ በሸሪዓ እይታ



ኔትዎርክ ማርኬቲንግ በሸሪዓ እይታ 
Gold Quest,DXN, Tiens..etc in Sharia view
(አጭር መልእክት በኢልያስ አወል)

ይህ መልእክት ከአምስት አመታት በፊት የተቀረፀ አጭር መልእክት ሲሆን በተለየያዩ መድረኮች ይህ የግብይት ሲስተም ብዙ ጎጂ ጎኖች እንዳሉት በተደጋጋሚ ቢገለፅም በዚህ ስራ ላይ የሚገኙ ሰባኪዎች ሰዎችን ጠልፈው የነሱ ሰራተኛ ለማድረግ የሚያደርጉት እልህ አስጨራሽ ጥረት ብዙዎችን እየሸነገለ ነውና ይህንን ቪዲዮ ሼር በማድረግ ከወዲሁ ሰዎችን ከጥቃት እንታደግ።


በዚህ ዙሪያ ረዘም ያለ ትምህርት ለሚፈልጉ ከታች በሚገኘው ሊንክ በቅርቡ የተለቀቀውን ረጅም ማብራሪያ ዳውንሎድ ማድረግ ይችላሉ።

⇊ ⇊ ⇊ ⇊
ኔትዎርክ ማርኬቲንግ በሸሪዓ እይታ (New Audio) 
በኢኮኖሚክስ ምሁሩ ወንድማችን ኢልያስ አወል የተሰጠ ሞያዊና ሸሪዓዊ ትንተና

Download link 

ኔትዎርክ ማርኬቲንግ... 
ጎልድ ኩዌስት... ቲያንሽ እና ሌሎችም ፒራሚዳዊ ይዘት ያላቸው የግብይት ዘዴዎችነ የሚጠቀሙ ድርጅቶችን ትክክለኛ አሰራር እና ኢስላማዊ ብያኔያቸውን ያብራራል።

- ኢስላማዊ የግብይት ደንቦችና ስርዓቶች ባጭሩ 
- የፒራሚድዊ ኔትዎርክ አስራር ምን ይመስላል?
- የኢኮኖሚ ጠበብቶችና አለም አቀፍ ተቋማት እንዴት ያዩታል?
- የኢስላም ሊቃውንት አቋም ምን ይመስላል?

ሌላም ብዙ ይማሩበታል...

ላይክና ሼር በማድረግ ወገንን እናድን!

ከዚህ አይንቱ ኔትወርክ ሰለባዎች ተሞክሮዎችን በኮሜንቶችን እንጠብቃለን

Pyramid network marketing schemes like Gold Quest,DXN, Tiens..etc
in Sharia view

by Ilyas Awol


https://www.facebook.com/tenbihat/videos/845476205549924/?fallback=1

Saturday, October 24, 2015

8ኛ ሓዲስ : ወደ ተውሒድ ጥሪ ማድረግ፥ ሙስሊም ክብር እንዳለው።





الحديث الثامن
الدعوة للتوحيد وبيان حرمة المسلم
عَنْ ابْنِ عُمَرَ رَضِيَ اللَّهُ عَنْهُمَا، أَنَّ رَسُولَ اللَّهِ صلىاللهعليهوسلمقَالَ: "أُمِرْت أَنْ أُقَاتِلَ النَّاسَ حَتَّى يَشْهَدُوا أَنْ لَا إلَهَ إلَّا اللَّهُ وَأَنَّ مُحَمَّدًا رَسُولُ اللَّهِ، وَيُقِيمُوا الصَّلَاةَ، وَيُؤْتُوا الزَّكَاةَ؛ فَإِذَا فَعَلُوا ذَلِكَ عَصَمُوا مِنِّي دِمَاءَهُمْ وَأَمْوَالَهُمْ إلَّا بِحَقِّ الْإِسْلَامِ، وَحِسَابُهُمْ عَلَى اللَّهِ تَعَالَى" .
رَوَاهُ الْبُخَارِيُّ [رقم:25]، وَمُسْلِمٌ [رقم:22].


8ኛ ሓዲስ

የሓዲሱ ትርጉም

ወደ ተውሒድ ጥሪ ማድረግ፥ ሙስሊም ክብር እንዳለው።

ተሚም ኢብን አውስ አድ-ዳርይ በዘገበው ሓዲስ የአላህ መልእክተኛ صلى الله عليه وسلم እንዲህ አሉ። “ሰዎች በእውነት የሚመለክ ጌታ አንድ አላህ ብቻ ነው ሙሓመድን የአላህ መልእክተኛ ነው ብለው እስኪመሰክሩ፥ ሶላትን ቀጥ አርገው እስከሚሰግዱ እና ዘካን እስኪያወጡ ድረስ እንድጋደላቸው ታዝዣሎህ። እነዚህን ነገሮች ካደረጉ ግን ደሞቻቸውን እና ገንዘቦቻቸውን የእስልምና ሓቅ ሲቀር ከእኔ ይጠብቃሉ። ሒሳባቸውም አላህ ዘንድ ነው።”

ሓዲሱን ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል።



ከስምንተኛው ሓዲስ የምንወስዳቸው ትምህርቶች

1. ወደ ተውሒድ ጥሪ ማድረግ እንዳለብን።

2. ዘካን አልሰጥም ያለ ጦርነት እንደሚከፈትበት።

3. አንድ ሰው ከላይ እስልምናን ካሳየ ስለውስጡን አያገባንም። ሂሳቡ አላህ ዘንድ ነው።

4. ሰው እንደስራው ይመነዳል።መልካም ከሰራ በመልካም መጥፎ ከሰራ በመጥፎ።

5. ሙስሊም ክብር(ደሙ፣ ንብረቱ፣ ክብሩ) እንዳለው። 

Friday, October 2, 2015

የሶላታችንን ነገር አደራ! (ክፍል አንድ)



የሶላታችንን ነገር አደራ!

(ክፍል አንድ)

(ኢብኑ ሙነወር፣ መስከረም 19/2008) 
 
 ሶላት የዲን ምሰሶ የአማኞች ብርሃን ናት፡፡ ሶላት ከሁለቱ ሸሃዳዎች ቀጥሎ ቀዳሚዋ የኢስላም መሰረት ናት፡፡ በሶላት ጭንቆች ይወገዳሉ፡፡ ፈተናዎች ይታለፋሉ፡፡ ሶላት ለነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የዐይን ማረፊያ፣ የእርካታቸው ቦታ ናት፡፡ ((ሶላት ከመጥፎና ከሚጠላ ነገር ሁሉ ትከለክላለች፡፡)) [አልዐንከቡት፡ 45] ሶላት ከላያችን ላይ ወንጀልን የምታረግፍ መጥረጊያ የሃጢኣት ቆሻሻን የምታፀዳ ወራጅ ውሃ ናት፡፡ [ሙስሊም]
ሶላት የማይሰግድ ሰው ምድቡ ከአማኞች ምድብ እንዳልሆነ የሚያመላክቱ እጅግ አስፈሪ የሆኑ ሐዲሦች ተላልፈዋል፡፡ እነዚህን ሐዲሦች መነሻ በማድረግም ሶላት የማይሰግድ ሰው “ሙስሊም ነው” “አይ አይደለም” በሚል በዑለማእ መካከል ጠንካራ የሀሳብ ልውውጥ አለ፡፡ አደጋ ላይ በመሆኑ ላይ ግን ቅንጣት ታክል ውዝግብ የለም፡፡ ኧረ እንዳውም “ሙስሊም ነው” ያሉት ሳይቀሩ “መገደል አለበት”፣ “መታሰር አለበት” … እያሉ ጥብቅ ሀሳብ የሰነዘሩት ቀላል አይደሉም፡፡ አንተ ከሶላት የተኳረፍከው ተላላ ሆይ! ይሄው የዲኑ ምሁራን “አንተ እጣ ፈንታህ ዘላለማዊ ቅጣት የሆነ ከሃዲ ነህ” በሚሉና “አይ ጥፋትህ ጫፍ የደረሰ፣ እጅግ አስፈሪ አደጋ የተደቀነብህ ጋጠ-ወጥ ሙስሊም ነህ” በሚል ጎራ ለይተው እየተወዛገቡብህ ነው!! ህሊና ካለህ ከዚህ በላይ ምን አስደንጋጭ ነገር አለ?!!
በርግጥ አሁን ርእሴ ከናካቴው ስለማይሰግድ ሰው አስፈሪ ሁኔታ መዘርዘር አይደለም፡፡ ይልቁንም የሶላት አሰጋገድ ህግና ደንቡን እንጠብቅ ዘንድ በስሱ ለማስታወስ ነው፡፡
አዎ መስገድ ብቻ ሳይሆን አሰጋገድን ማሳመርም ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ጌታችን አላህ ((ለሰጋጆች ወዮላቸው!)) ማለቱን አንዘንጋ፡፡ አዎ ((ለነዚያ ከሶላታቸው ተዘናጊዎች ለሆኑት!!)) [አልማዑን፡ 4-5] መልእክተኛው ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የሶላት አሰጋገድን በቃልም አስተምረዋል፣ በተግባርም አሳይተዋል፡፡ ለዚህም ሲሉ ሚንበር ላይ ወጥተው እስከሚሰግዱ ደርሰዋል፡፡ ሚንበሩ ላይ ይቆማሉ፣ ሩኩዕ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ካጠናቀቁ በኋላ “ይህን የሰራሁት በኔ እንድትመሩ ነው፡፡ አሰጋገዴንም እንድትማሩ” ብለዋል፡፡ [ቡኻሪና ሙስሊም] እንዳውም ሶላትን በስርኣት ለሰገደ ከአላህ ብስራት ነግረውታል፣ እንዲህ ሲሉ፡- “አምስት ሶላቶችን በርግጥም አሸናፊውና የላቀው አላህ ደንግጓቸዋል፡፡ ውዱኣቸውን ያሳመረ፣ በወቅታቸው የሰገደ፣ ረኩዓቸውን፣ ሱጁዳቸው እና ኹሹዐቸውን ያሟላ ሰው በአላህ ላይ ሊምረው ቃል አለው፡፡ (እንዲህ) ያላደረገ ግን በአላህ ላይ ቃል የለውምና ከፈለገ ይምረዋል፣ ከፈለገም ይቀጣዋል፡፡” [ቡኻሪ]
አዎ የምናገኘው ያስገኘነውን ያክል ነው፡፡ “ሶላት መለኪያ ነች፡፡ መለኪያውን የሞላ ይሞላለታል፡፡ መለኪያውን ያጓደለ ግን ስለ ስፍር አጉዳዮች ምን እንደተባለ ታውቃላችሁ” ይላሉ ሰልማን አልፋሪሲ፡፡ ቀደምቶቻችን ከአንድ ሰው ዒልም ሊወስዱ ሲፈልጉ ቀድመው አሰጋገዱን ይመለከቱ ነበር፡፡ ሶላቱን በስርኣት ሲፈፅም ከተመለከቱት እሰየው! ካልሆነ ግን ለሶላቱ ታማኝ ያልሆነን ሰው እጃቸውን ከሱ ይሰበስቡ ነበር፡፡ በርግጥም ሶላት የአንድ ሙስሊም ስብእና ቀዳሚ መለኪያ ነች፡፡
እናም ለሶላታችን በምንሰጠው ዋጋና አፈፃፀም ልክ የምናገኘውም ደሞዝ ይለያያል፡፡ ይህን አስመልክተው ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ይላሉ፡- “በእርግጥም አንድ ባሪያ ሰላትን ይሰግድና ነገር ግን ከሷ አንድ አስረኛዋ (ወይም) አንድ ዘጠነኛዋ (ወይም) አንድ ስምንተኛዋ (ወይም) አንድ ሰባተኛዋ (ወይም) አንድ ስድስተኛዋ (ወይም) አንድ አምስተኛዋ (ወይም) አንድ አራተኛዋ (ወይም) ወይም አንድ ሶስተኛዋ (ወይም) ግማሹዋ እንጂ አይፃፍለትም” ይላሉ፡፡ [አልባኒ ሶሒሕ ብለውታል] ስለዚህ እንደ አሰጋገዳችን መለያየት የምናስመዘግበውም ምንዳ ይለያያል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ከሶላታችን በደንብ መጠቀም እንችል ዘንድ አሰጋገዳችንን ከነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም አሰጋገድ ጋር ለማመሳሰል መጣር ይጠበቅብናል፡፡ ለዚህም “ስሰግድ እንዳያችሁኝ ስገዱ” የሚለው የነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም መመሪያ ጥሩ ዋቢ ይሆነናል፡፡ [ቡኻሪ]
በአንድ በወቅት ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከመስጂዱ አንድ ጥግ ላይ ሳሉ የሆነ ሰው መስጂድ ገባና መስገድ ያዘ፡፡ ሶላቱን ግን በጣም አሳጠራት፡፡ ሲጨርስም ከነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ዘንድ መጣና ሰላምታን አቀረበ፡፡ እሳቸውም “ወዐለይከስሰላም፡፡ ተመለስና ስገድ፣ ምክንያቱም አንተ አልሰገድክምና” አሉት፡፡
ተመለሰና ሰገደ፡፡ ከዚያም ሰላምታ አቀረበ፡፡
አሁንም “ወዐለይከስሰላም፡፡ ተመለስና ስገድ፣ ምክንያቱም አንተ አልሰገድክምና” አሉት፡፡
በሶስተኛው ጊዜ ሰውየው እንዲህ አለ፡- “በሐቅ በላከህ ይሁንብኝ! ከዚህ ውጭ ማሳመር አልችልም፡፡ ስለሆነም አስተምረኝ” አላቸው፡፡
ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ አሉት፡- “ለሶላት ስትዘጋጅ
ውዱእህን አሳምር፤
ከዚያም ወደ ቂብላ ተቅጣጭ፤
ከዚያም ‘አላሁ አክበር’ በል፤
ከዚያም ከቁርኣን የተገራልህን ቅራ፤
ከዚያም ሩኩዕ አድርግ፣ በሩኩዑህ ላይ እስከምትረጋጋ ድረስ፤
ከዚያም እራስህን (ከሩኩዕ) አቅና፣ ተስተካክለህ እስከምትቆም ድረስ፤
ከዚያም ሱጁድ ውረድ፣ በሱጁድህ ላይ እስከምትረጋጋ ድረስ፤
ከዚያም ከሱጁድ ተነስ፣ ቀጥ ብለህ እስከምትቀመጥ ድረስ፤
ከዚያም ሱጁድ ውረድ፣ በሱጁድህ ላይ እስከምትረጋጋ ድረስ፤
ከዚያም ተነስ፣ ተስተካክለህ እስከምትቆም ድረስ፤
ከዚያም ይህን (መረጋጋትህን) በሶላትህ በሙሉ ላይ ፈፅም፡፡
[ቡኻሪ፣ ሙስሊም፣ ኢብኑ ማጃህ፣ አልበይሀቂ፣…]
ከዚህ ክስተት እና የነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እርማት ብዙ ቁም ነገሮችን መማር እንችላለን፡፡ ከምንም በላይ ግን “አልሰገድክም ተመለስ ስገድ” እያሉ ማመላለሳቸውን እናስምርበት፡፡ ከራሳችን ሶላትም ጋር እናነፃፅረው፡፡ በጥቅሉ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ስሰግድ እንዳያችሁኝ ስገዱ” ያሉት፡፡ [ቡኻሪ] ሶላታችንን ከሳቸው ሶላት ጋር ለማመሳሰል አሰጋገዳቸውን ጠንቅቆ ማወቅ ይጠይቃል፡፡ አሰጋገዳቸው በተለያዩ የሱናህ ኪታቦች ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ በተለይም ደግሞ “ሲፈቱ ሶላቲንነቢይ” የሚለው የታላቁን ሙሐዲሥ የሸይኹልአልባኒይ ረሒመሁላህ ኪታብ በዚህ ረገድ እፁብ ድንቅ የሆነ ስራ ነው፡፡ እባኮትን በጥሞና አንብበው አሰጋገደዎን ይታዘቡ፡፡ በተግባርም ይጠቀሙት፡፡ ሌሎችንም ያስጠቅሙ፡፡ በአላህ ፈቃድ ከዚህ ኪታብ እና መሰል ስራዎች እየቀነጨብኩ እጅግ አንገብጋቢ ናቸው ብየ የማምንባቸውን በተከታታይ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡

(ኢብኑ ሙነወር፣ መስከረም 19/2008)
 
 

Saturday, September 5, 2015

“በመካሪነት በኩል ሞት በቃ!” ይባል ነበር ድሮ



“በመካሪነት በኩል ሞት በቃ!” ይባል ነበር ድሮ

(ኢብኑ ሙነወር፣ ነሀሴ 26/2007)
 

ድሮ ድሮ ዘመድ ወዳጅ ሲሞት አገር ሁሉ ያዝን ይጨነቅ ነበር፡፡ የአንዱን ወዳጅ ሞት ተከትሎ የሞትን አስፈሪነት፣ የዱንያን አላቂነት እዚህም እዚያም የሚያወሳው ስለሚበዛ አዋቂ ቀርቶ ልጆች እንኳን ሳይቀሩ ከውስጣቸው ፍርሃት ይሰፍን ነበር፡፡ አንድ ሰው ጣእረ-ሞት ላይ መሆኑ ሲሰማ አገር ይጨነቃል፡፡ ሞቱ ሲሰማ ደግሞ አገር በድንጋጤ ይዋጣል፡፡ ከቀብር መልስ ደግሞ ሌላ የሀዘን ድባብ፣ ሌላ “ዋ! መጨረሻችን፡፡” የቀብር ጥያቄን፣ የቂያማ አስፈሪ ሁኔታን እያሰላሰለ በስጋት የሚዋጠው ቀላል አልነበረም፡፡ የዘነጋ ካለም በትንሽ ማስታወሻ ቅስሙ ይሰበራል፣ በድንጋጤ ይዋጣል፣ ውስጡ ሁሉ ይረበሻል፡፡ ለአፍታም ቢሆን ባለበት ሁኔታ ሞት ድንገት “እጅ ወደላይ” እንዳይለው በመስጋት ወደ ጌታው ይመለሳል፣ ዐውፍ ይባባላል፣ አማናን ይመልሳል፣ ሶላቱን እንደ አዲስ ይጀምራል፣ ሌላም ሌላም፡፡ ዛሬ ግን ትላንት አይደለም፡፡ ሞት ባይቀርም ሞትን ተከትሎ መቶበት ግን ምናልባት ካልቀረ ቀሏል፡፡ ሞት ቢበዛም በሞት አኺራን ማስታወስ ግን መንምኗል፡፡ ወዳጃችንን፣ ወገናችንን ከዒባዳው አለም ከፈተናው አለም ወደ ደሞዝ አለም፣ ወደ ጥያቄው አለም እየሸኘነው እንኳን ቡድን ቡድን ሰርተን እናሽካካለን፣ ምንም እንዳልተፈጠረ፣ ምንም እንደማይጠብቀን፣ ያለ ይሉኝታ፣ ያለ ሐያእ፣ እናወራለን፣ እናወራለን፣ እናወራለን፡፡ እያወራንም እንገለፍጣለን፡፡ አስከሬን ከአፈር በታች እየገባም ያለምንም “ነግ በኔ” ድምፃችንን ከፍ አድርገን ከጓደኛ ጋር ወይም በስልክ ስለ ቢዝነስ እናወራለን፣ ቢዝነስ! ቆመን ተቀምጠን ቢዝነስ! እየሰገድን የምናስበው ቢዝነስ! ስንተኛ ስንነሳ እንደ ዚክር የሚታወሰን ቢዝነስ! ወደ ሀብት እሽቅድድም!! ሀያሉ “በብዛት መፎካከር (ጌታችሁን ከመገዛት) አዘናጋችሁ፡፡ መቃብሮችን እስከምትጎበኙ (እስከምትሞቱ) ድረስ” ማለቱ ምንኛ አስፈሪ ሐቅ ነው፡፡ “ተከልከሉ” እያለ ነበር፡፡ ግና ማን ይስማ? ልብ ከተዘጋ ጆሮ በድን ነው፡፡
ሱብሓነላህ! መዘናጋታችን እጅጉን ለከት አጥቷል፡፡ ሞቱ የራሳችን የቤተሰባችን ከሆነም የወግ የባህሉ እንዳይቀር ስለተለየን ስጋ ዋይታ ከማሰማታችን ባለፈ ለሸሪዐው ህግና ደንብ እጅ የምንሰጠው ስንቶቻችን ነን? በሱናው አናካትምም፣ በሱናው አንገንዝም፣ በሱናው አንሰግድም፣ በሱናው አንደፍንም፣ በሱናው አንፅናናም፡፡ አዎ እነዚህ ነገሮች በአብዛሀኛው እንዳሉን ይገባኛል፡፡ ነገር ግን ላቀበሉን አባቶች አላህ ውለታቸውን ይክፈላቸውና በውርስ ከመቀበላችን ውጭ በውስጣቸው ስለሚገኙ እርማት ስለሚሹ ነገሮች ግን ትኩረታችንም አይደለም፡፡ ማካተሙን፣ መገነዙን፣ መድፈኑን ወዘተ በኪታብ ከሚቀራውና ከሚያስተምረው ቃልቻ ይልቅ በውርስ ያገኘው የኔ ብጤ ጃሂል ነው በአብዛሀኛው የሚያከናውነው፡፡
ወደ ነገሬ ስመለስ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዳሉት ዛሬ ሞት እጅጉን በዝቷል፡፡ ሰው ዛሬ በየእለቱ እንደቅጠል ይረግፋል፡፡ እያወራ ይሞታል፣ እየሄደ ይሞታል፣ በተኛበት ይሞታል፣ ስሙ እጅጉን በበረከተ የህመም አይነት ይሞታል፣ እንደ ዋዛ ከቤቱ ወጥቶ ይቀራል፡፡ የዜና አውታሮች አብዛሀኛው ሽፋናቸው ሞት ነው- አይነቱ የበዛ እልቂት፡፡ እጅጉን ከመብዛቱ፣ በዱንያም ከመጠመዳችን የተነሳ ጆሯችን በሞት ዜና አይሳቀቅም፡፡ ልባችንም ደንድኗል አይደነግጥም፡፡ ግና ከመብዛቱ የተነሳ ብዙም ሳይደንቀን የምንሰማው ሞት ከአፍታ ወይም ከዘመናት በኋላ ተረኞች እንንደምንሆንበት እሙን ነው፡፡
እርግጥ ነው በዱንያ መልካምን የሚሰራ፣ ለበጎ ስራ የሚታትር፣ ለኢኽላስ የሚጨነቅ፣ ጧት ማታ ጌታውን የሚያወሳ አካል ሞትን አይፈራም፣ አይጠላውምም፡፡ ምክንያቱም በሞት እርባና ቢሷን ዱንያ ተሰናብቶ ዘላለማዊቷን ሀገር ያልማልና፡፡ ሞትን አይፈራም፡፡ ከፀጋዎች ሁሉ በላጭ ፀጋ የሆነውን ጌታውን መመልከትን ይናፍቃልና፡፡
ነገር ግን የቂናችን በመድከሙ፣ የዱንያ ፍቅራችን በማየሉ፣ ለመኖር ያለን ጉጉት ወሰን አልባ በመሆኑ ሳቢያ ሞትን እንጠላለን፡፡ ስለምንጠላም እውነተኛው አይቀሬው ሞት ከመምጣቱ በፊት ብዙ ጊዜ እንሞታል፡፡ አዎ ደግመን ደጋግመን በጭስ አልባ ሽብር እንሞታለን፡፡ በሽብር እንደ ጨው እንሟሟለን፣ እንደ በረዶ እንቀልጣለን፡፡ ሽብር ስል አጥፍቶ መጥፋት ማለቴ አይደለም። ሽብር ማለቴ ስለ አይ ኤስ ወይም አልቃኢዳም አይደለም። የማወራው ከአይኤስ ከአልቃኢዳ የሚያስከነዳ ሽብር እየፈፀሙ በሽብር ስም ስለሚነግዱት እስራኤል፣ አሜሪካና ተባባሪዎቻቸውም አይደለም። ሽብር ስል እያሸበሩ በሽብር ስለሚነግዱትም አይደለም፡፡ የማወራው ለዱንያ ያለን ፍቅር ገደብ በማጣቱ ሳቢያ የእያንዳንዳችንን ቤት እያንኳኳ ስላለው ሽብር ነው። የማነሳው ሞትን እጅጉን ከመጥላታችን የተነሳ እያርበደበደን ስላለው ሽብር ነው። አዎ አንድ ጥይት ሳይተኮስ አንድ ቦንብ ሳይፈነዳ በፍርሃት እያራደን ያለው ሽብር። ይሄኛው ሽብር ዘር ከሃይማኖት አይመርጥም። ይሄኛው ሽብር በሰው አልባ ድሮን በብረት ለበስ ታንክ አይወደምም። ይሄኛውን ሽብር ጓንታናሞ አቡ ገሪብ አስገብቶ ቁም ስቅሉን ማሳየት አይቻልም። ይሄኛው ሽብር በተቀነባበረ ክስ በሀሰት ምስክርም አይገላገሉትም።
አሸባሪው ገና ከርቀት ስናየው በስጋት መንገድ የምንለቅለት ቀይ ሽብሩ ሲኖ ትራክ (ሲኖ ጭራቅ) አይደለም። ሽብሩ ደም ግፊት ነው፣ እስትሮክ ነው። ሽብሩ ካንሰር ነው፣ የስኳር ህመም ነው፣ ኤች አይ ቪ ኤድስ ነው። ሽብሩ ጉበት ነው ኩላሊት ነው። ዛሬ “የጉበት ህመም አለብህ” ስለተባለ ብቻ የጨው አምድ የሚሆነው ቀላል አይደለም፡፡ ዛሬ “ካንሰር አለብህ” ስለተባለ ብቻ ተስፋ ቆርጦ እራሱን የሚያጠፋው ጥቂት አይደለም፡፡ ዛሬ “ስኳር አለብህ” ስለተባለ ብቻ የሚያየው ሁሉ ጨለማ የሚሆንበት አንድ ሁለት አይደለም፡፡ ታዲያ ከዚህ በላይ ምን ሞት አለ? የትኛውስ በሽታ ባይይዝህ ሞት ሊቀር ነውን? ታዲያ ይሄ ሁሉ ሽብር፣ ይሄ ሁሉ ተስፋ መቁረጥ ለምን? “ሞት ላይቀር ማንቋረር” ያለው ማን ነበር? አትጠራጠር ሞት ሁሉም የሚጎነጨው ፅዋ ነው። የሞትከው የተወለድከ እለት ነው፡፡ አለቀ!! ጌታችን አላህ፡ “ነፍስ ሁሉ ሞትን ቀማሽ ናት።” “የትም ብትሆኑ በጠነከሩ ህንፃዎች ውስጥ ብትሆኑም እንኳን ሞት ያገኛችኋል” ይላል፡፡ ይልቅ የዘነጋነው ሌላ ሞት አግኝቶናል፡፡ ይልቅ ያላስተዋልነው ሌላ ሙሲባ ወድቆብናል፡፡ መልክና አምሳያ የሌለው ሞት!! የልብ ሞት!! ከዚህ በላይ ምን ሞት አለ? ሱፍያን አሥሠውሪይ ረሒመሁላህ “በሰዎች ላይ ልቦች ሞተው አካላት ህያው የሚሆኑበት ዘመን ይመጣል” ይላሉ፡፡ አላሁልሙስተዓን!! ይሄው ልባችን ሞቶ በድናችን ቀርቷል፡፡ ኢና ሊላሂ ወኢና ኢለይሂ ራጂዑን! “ለአኺራየስ ምን ተዘጋጅቻለሁ?” ብሎ በመጨነቅ ፋንታ ቀልባችንን ለገደለችው ዱንያ ስንል ተስፋ እንቆርጣለን፡፡ ሌላ ሞት፡፡ እራስን ማጥፋት!! ብልጦች እንደሆንን እናስባለን፡፡ ግና ሲበዛ ቂሎች ነን፡፡ ከዘላለማዊ ህይወቱ ይልቅ አላፊ ቆይታን ካስቀደመ ሰው በላይ ማን ቂል አለ?! “ብልጥማ እራሱን የተቆጣጠረው ነው፣ ከሞት በኋላ ላለ ህይወቱ የተጋው፡፡”
ድሮ ከታላላቆቹ ሶሐብዮች ዐብዱላህ ኢብኒ መስዑድ እና ዐማር ኢብኑ ያሲር ረዲየላሁ ዐንሁማ ተይዞ "ከመካሪነት በኩል ሞት በቃ!" የሚል ልብን ዘልቆ የሚነካ መልእክት ተላልፎ ነበር። በርግጥ ሰነዱ ዶዒፍ መሆኑ እንጂ ከነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በማገናኘትም የተላለፈበት አለ። ዝርዝረሩን የሸይኹልአልባኒን ረሒመሁላህ አድዶዒፋህ ኪታብ ቁጥር: 502 ይመልከቱ። ብቻ ከሶሐቦቹ የተገኘው ትውፊት ለመማማር በቂያችን ነው። እውነትም እንደሞት ማን መካሪ ነበር!? ሞት ያላስተማረው ሰው በምን ይማራል? ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም "ጥፍጥናዎችን ቆራጭ የሆነውን (ሞትን) ማስታወስን አብዙ" ማለታቸው ለዋዛ አልነበረም። ምን ዋጋ አለው ዛሬ ከሞትም የምንማረው ጥቂቶች ሆነናል። በቤተሰባችን፣ በጓደኛችን ሞት ከማዘን ከማንባት በዘለለ "ድንገት ተረኛ ብሆንስ?" ብለን ተጨንቀን ላፍታ እንኳን የቀብር ህይወትን፣ ቂያማን፣ ሲራጥን፣ ሚዛንን ወዘተ አስታውሰን በመዘናጋታችን የደነገጥነው ከሰመመናችን የነቃነው ስንቶቻች ነን?
እኩይ ምግባርን ባህሪህ ያደረግከው ወገኔ ሆይ ከፊትህ ሞት አለ። የሰው ሐቅ ያለ አግባብ የምትነጥቀው ብልጥ መሳዩ ቂል ሆይ ከፊትህ ሞት ተደቅኗል። ሃሜተኛው ነገረኛው ፍጥረት ሆይ የስራህን ታጭድ ዘንድ ሞት ከፊትህ እየጠበቀህ ነው። በሶላትህ የምትቀልደው የምትዘናጋው ቦዘኔ ሆይ! ዘላለማዊ ቁጭትን የሚያወርስህ ሞት ተደግሶልሃል። የወላጆችህን ሐቅ የምትጥሰው አደራ በላ ሆይ ዛሬ ነገ ሳትል በፍጥነት እራስህን አስተካክል፣ ከጌታህ ጋር ታረቅ፡፡ በጥቅሉ ለጌታህ ለዲንህ ጀርባህን የሰጠኸው ዝንጉ ሆይ! ሞት ወደ አንተ እየመጣ ነው፡፡ ወንድሜ ሆይ እህቴ ሆይ ወደ ጌታችን እንመለስ፡፡ ጧት ማታ ሞትን እናስታውስ፡፡ አንዱ ዓሊም እንዲህ ይላሉ፡ “ሞትን ማስታወስን ያበዛ ሰው ሶስት ነገሮችን ይታደላል፡፡ እነሱም ተውባን ማፋጠን፣ የልብ መብቃቃት እና ለዒባዳህ መነሳሳት፡፡ ሞትን የረሳ ደግሞ በሶስት ነገሮች ይቀጣል፡፡ ተውባን እየተዘናጉ ማሳለፍ፣ ባለ አለመብቃቃት እና ከዒባዳህ መዘናጋት፡፡” እስኪ እራሳችንን እንገምግም፡፡ ሞት አማክሮ አይመጣምና በተጠንቀቅም እንሁን፡፡ ኢብኑ ዑመር ረዲየላሁ ዐንሁ “ካመሸህ ንጋትን አትጠባበቅ፡፡ ካነጋህ ደግሞ ምሽትን አትጠባበቅ፡፡ በጤናህ ጊዜም ለህመምህ ጊዜ የሚሆንህን፤ በህይወት ሳለህም ስትሞት የሚሆንህን ያዝ” ይላሉ፡፡ በጥፋት የምንጠምዳቸው የአካል ክፍሎቻችን በኛ ላይ ምስክር ከመሆናቸው በፊት እንንቃ፡፡ ሞት የትና መቼ እንደሚይዘን አናውቅምና አዋዋላችንን እናሳምር፣ ባስቸኳይ ወደ አላህ እንመለስ፡፡ ጌታዬ ሆይ ይቅር በለን። አንተን በማስታወስ፣ አንተን በማመስገን፣ አንተን ባማረ መልኩ በመገዛትም ላይ አግዘን።
አንተ የቆምከው ከቀብሬ
አትደነቅ በነገሬ
እንዳንተው ነበርኩኝ ትላንት
የዘነጋሁ ከዚህ መዐት
ይልቅ ተመከር አንሰራራ
ነገ አንተ ነህ ባለ ተራ፡፡

(ኢብኑ ሙነወር፣ ነሀሴ 26/2007)
 

Wednesday, July 29, 2015

እህቴ ለምን ይሆን ይህን መልበስሽ?



ከ ወንድም Sultan Khedir የተወሰደ።

እህቴ ለምን ይሆን ይህን መልበስሽ?
የምእራባውያንን መንገድ መከተልሽ?
የተወዳጆቹን ምእመናት ልብስ መተውሽ?
እኮ ለምን?
እነርሱ እኮ ለኢስላም ያላቸውን ጥላቻም እያንፀባረቁ ይሆናል፣ይህንን ተገንዝበሻል?
በነፃነት ስም እርቃንሽን እንዳስኬዱሽ፣እንዳስቀሩሽ?
መለስ በይ ወደ ጌታሽ
ሞት እንደሆነ እድሜሽን ሳይጠይቅ፣
ምክኒያት ሳይፈልግ ያንኳኳል በርሽን በድንገት ሊወስድሽ፣
ታዲያ ለምን ይሆን መልበስሽ?
ጌታሽ ፊት ቆመሽ ስትጠየቂ?ስትተሳሰቢ
ጌታሽ ለምን እንደለበሽው ምክኒያቱን ሲጠይቅሽ
በተመለከተሽ ወጣት ዓይን ልክ
እርቃንሽን ባየሽ ሰው መጠን
ያኔ ለምን ለበሽ ? ስትባይ
መልስ የለሽም ከፀፀት በቀር
አስቢበት ዱንያ ምን ብታስደስት አጭር እና ጠፊ ነች።
ተመለሽ ጊዜው ሳያልፍ ፀፀት የማይጠቅምበት ጊዜ
ከመምጣቱ በፊት፣
 

Thursday, June 4, 2015

7ኛ ሓዲስ - ዲን መመካከር ነው።










الحديث السابع

"الدين النصيحة"

عَنْ أَبِي رُقَيَّةَ تَمِيمِ بْنِ أَوْسٍ الدَّارِيِّ t أَنَّ النَّبِيَّ صلى الله عليه وسلم قَالَ: "الدِّينُ النَّصِيحَةُ. قُلْنَا: لِمَنْ؟ قَالَ لِلَّهِ، وَلِكِتَابِهِ، وَلِرَسُولِهِ، وَلِأَئِمَّةِ الْمُسْلِمِينَ وَعَامَّتِهِمْ" .
رَوَاهُ مُسْلِمٌ [رقم: 55].

7  ሓዲስ

የሓዲሱ ትርጉም

ዲን መመካከር ነው።

ተሚም ኢብን አውስ አድ-ዳርይ በዘገበው  ሓዲስ ነብዪ صلى الله عليه وسلم  እንዲህ አሉ። “ዲን መመካከር ነው።” ለማን በማለት ሱሓቦች ጠየቁ። እሳቸውም ለአላህ፣ ለመጽሃፉ፣ ለመልእክተኛው፣ ለሙስሊሙ መሪዎች እና ለአጠቃላይ ሙስሊሙ ነው በማለት መለሱ።
ሓዲሱን ሙስሊም ዘግቦታል።

ከሰባተኛው ሓዲስ የምንወስዳቸው ትምህርቶች
1.     ዲን ሁሉ በምክክር የተገደበ እንደሆነ።
2.     መመካከር ለአላህ፣ ለመለአክተኛው መሓመድ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም)፣ ለሙስሊም መሪዎች፣ እና ለተራው ሙስሊም እንደሆነ።
3.     በምክክር ላይ እንደገፋፋ።
4.     ማጭበርበር(የመመካከር ተቃራኒ ስለሆነ) የተከለከለ እንደሆነ።



Saturday, May 9, 2015

~`~ትዳርህን ተንከባከበው~`~



~`~ትዳርህን ተንከባከበው~`~

የአጋርህን ስሜት ተረድተህ
ሃላፊነትህን ተወጣ
°°°°°°° ✅ °°°°°°°


የተንቢሃት ልዩ ሳምንታዊ መልዕክት ቁ• 11

① ስሜትን መረዳት

ትዳር በህይወታችን ውስጥ ከፍተኛውን ሚና የሚጫወት ሲሆን የግለሰብ፣ የቤተሰብና የማህበረሰብ ኣልፎም ያጠቃላይ የሰው ልጆች መገንቢያ ማዕከል ነው።

በትዳር ዓለም በሌሎች የህይወት ዘርፎች የማይገኙ ክቡር ትሩፋቶች ይገኙበታል።

√ እውነተኛ አፍቃሪ
√ ሚስጥረኛ ወዳጅ
√ ከማንም የቀረበ ነውርን ሸፋኝ
√ የተባረከ ተተኪ ትውልድ
√ ቤተሰብ፣ አዳዲስ ዘመዶች…
√ ሀላል የሆነ እርካታ
√ የኔ ሚባል ደጋፊ እና የመሳሰሉት

ይህ እጅግ በጣም ብዙ ጥቅሞች ያሉበት ትዳር የሚባለውን ፕሮጀክት በአግባቡ ለመምራትና የሚጠበቀውን ጥቅም ለማግኘት ወሳኝ ከሚባሉት ነጥቦች ኣንዱ የትዳር ጓዶቹ መግባባት ነው።

መግባባት ደግሞ የሚወለደው ኣንዱ ያንዱን ስሜትና ፍላጐት ሲገነዘብና አስፈላጊውን ምላሽ ሲሰጥ ነው።

ለዚህም ማስተዋያ እንዲሆነን የአርዓያችንን የህይወት ታሪክ ስናስተውል ከምእመናን እናት ዓኢሻ ቢንቱ ሲዲቅ ረዲየላሁ ዐንሁም ጋር ሳሉ የገጠማቸውን ሲነግሩን እንዲህ ይላሉ።

ሙስሊም በዘገቡት ትክክለኛ ሀዲስ ዓኢሻ ረዲየላሁ ዐንሃ በሆነ ጉዳይ ቅር ሲላት ወይም ደስተኛ ስትሆን ያውቁባት ነበር።

በዚህም ጥናታቸው ባለቤታቸው በመሃላዋ ውስጥ እንኳን ቅሬታዋን የምትገልፅበትን መንገድ በተከታዩ መልክ ገልፀዋል።

« በኔ ላይ ደስተኛ ስትሆኚም ሆነ በኔ ላይ ስትቆጪ አውቃለሁኝ።

በኔ ላይ ደስተኛ በሆንሽ ግዜ 
በሙሐመድ ጌታ ይሁንብኝ " ትያለሽ።

በኔ ላይ በተቆጣሽ ግዜ ደግሞ:
በኢብራሂም ጌታ ይሁንብኝ " ትያለሽ ። »

ቁጣዋንና ደስታዋን ለይተው እንደሚያውቁት እየገለፁ ነው።

አስተውሉ!

ዓኢሻ ረዲየላሁ ዐንሃ ክፉ ቃል አልወጣትም፣ ጮሃም ተንጫጭታም በቁጣ አልተናገረችም። ነገር ግን በሳቸው ላይ ቅር ስተሰኝ አጋጣሚ መሃላ የሚያስፈልገው ጉዳይ ሲገጥማት በስማቸው መማልን ታኮርፍና በነቢዩ ኢብራሂም ጌታ ይሁንብኝ ትላለች።

ቁጣዋ ሲለቃት ግን በሙሐመድ ጌታ ይሁንብኝ ስትል ትምላለች።

ይህንንም ባህሪዋን መልእክተኛው አወቁባትና ነገሯትም።

ስለዚህም የትዳር አጋሮቻችንን ስሜት እዚህ ድረስ ለይቶ ለማወቅ የቅርብ ክትትል ማድረግህ እቤትህ ያለውን ችግር ለመረዳት ራስህንም፣ እሷንም ለማረም ይረዳሃል።

የአላህ መልእክተኛ ﷺ ውዷ ባለቤታቸው ዓኢሻ ቢንት አቢ በክርም ሆነች ሌሎች የምእመናን እናቶች (ረዲየላሁ ዐንሁነ አጅመዒን) በሆነ ጉዳይ ቅር መሰኘታቸውንና ኣለመሰኘታቸውን በትኩረት ይከታተላሉ ይረዱታልም።

እኛም አርዓያነታቸውን አምነን እስከተቀበልንና በተግባር ማዋሉም ተገቢ እንደሆነ እስካመንበት ድረስ፤ ለትዳራችን ስኬት ግራ ቀኝ ብለን ሌላ መፍትሄ ከምናፈላልግ ወይም እያቋቋምን ከምናፈርስ ወደ መመርያችን እንመለስ።

ትዳር ሲባል :

~ ቤት መመስረት፣
~ ገብቶ መብላት፣
~ ለብሶ መውጣት፣
~ ደርሶ መተኛትና
ልጅን መውለድ ብቻ አይደለም።

የራሱ የሆነ ለየት ያለ ዓለም ከመሆኑ አንፃር ጣዕሙና ለዛውም እንደየ ባለትዳሮቹ ይፈራረቃል።

በተሰማራህበት መስክ

•> ህዝብን የምትቀርፅ ሸይኽ ብትሆን፣ 
•> ቀን ከሌት የምትገስፅ ዳዒ ብትሆን፣ 
•> ከሆነ አመራር ድርሻ ቢኖርህ፣
•> ታታሪ ነጋዴም ብትሆን፣
•> ባለ ዓላማ ተማሪ ብትሆን፣
•> ተመራማሪም አጥኚ ብትሆን፣
•> ኑሮን ምትታገል ቅጥረኛም ብትሆን… …

እቤትህ የተገነባው በነበልባል ከሆነ በተለያዩ ክስተቶች እርር… ድብን… ቅጥል የምትልበት እድሉ ስለሚሰፋ ሌሎች ዓላማዬ ብለህ የተነሳህለትን ጉዳዮችህን በተግባር ማዋል የማትችል ትሆናለህ።

ለብሰህ ሲያዩህ የተመቸህ ምሰል እንጂ አቅልህ በሆነ ነገር ርቆሃል።

እንደው ፈገግ ስትልና እኩል ስታወራ የተደላደልክ ብትመስልም ዘወር ስትል የምትተነፍሰው እሳት ነው።

በቆምክበት መድረክ ሁሉ የተረበሽክ ስለምትሆን ብዙ ነገርህ ይምታታል።

የዛሬው ስራህን መገምገሚያ፣ ለነገው ፕሮግራምህ መዘጋጃ የሚሆን ሰላማዊ ቤት ስለሌለህ የቆምክለት ጉዳይም ቤትህም ስልችት ይሉሃል።

የራስህንም ሆነ የባለቤትህን ማንነት በጥልቅ ስላልተረዳህ ጥፋትህን መደበቂያ ሰበብ ፈላጊ ትሆናለህ።

ሁሌም ተሰቃየሁ እንጂ አሰቃይቼ ይሆን ብለህ ራስህን አትገመግምም።

በዚህም ሰበብ ወደቤትህ በመጣህ ቁጥር እሷን ማሸነፍያ ቃላቶችን ስታሰላስል አእምሮህን ወጥረህ…… መሆን የሚገባህንና መስራት የነበረብህን በርካታ ነገሮች ትዘላቸዋለህ።

ሰላም የሌለው ትዳር ማለት የበሽታዎች ሁሉ በሽታ ነው። ያውም ታማሚውና አስታማሚው እኩል የተያዙበት በሽታ።

የዚህ ሁሉ አብዛኛው ሰበቡ አንተው ትሆናለህ።

ሰበብ አታፈላልግ ስህተቷን ብቻ አታጉላ! በደልንም ፍራ!

°°°°°°°✅°°°°°°

ጥቂት የማይባሉ እንስቶች ብዙውን ግዜ በንጭንጬ፣ በጩኸት፣ በችኮላና፣ በቁጣ ሃሳባቸውን ይገልፁ ይሆናል።

ብሶታቸውንም በስድብ፣ በእርግማን፣ በወቀሳና በለቅሶ ያሳዩም ይሆናል።

የዚህን ግዜ ከውጭ ለሚመለከት ታዛቢ ሁለት ነገሮችን ያንፀባርቅለታል።

~ ወይ በጣም የተበደለች
~ ወይ ደግሞ አስቸጋሪ ሚስት ነች የሚል ጥርጣሬ ላይ ያደርሰዋል።

እውነታው ግን አንተጋ ግልፅ ነው። ተበዳይነቷም ሆነ አስቸጋሪነቷ እዚህ ደረጃ ሳይደርስ ማከም የምትችልበት ስልጣንና መፍትሄዎች ሁሉ ተሰጥተውሃል።

ከዚያ ያለፈ ነገር ሆኖ መለያየት ቢከሰት እንኳ ቀድመህ የሚጠበቅብህን ከተወጣህ የሚቆጭህ አትሆንም።

ለሷም የእድሏን ላንተም የድርሻህን የሚሰጥ አምላክ እኮ ነው ያለን። የምን በራስም በሰውም ህይወት መቀለድ ነው

قال تعالى: (وَإِن يَتَفَرَّقَا يُغْنِ اللّهُ كُلاًّ مِّن سَعَتِهِ وَكَانَ اللّهُ وَاسِعًا حَكِيمًا) النساء 130

« ቢለያዩም አላህ ሁሉንም በችሮታው ያብቃቃቸዋል። አላህም ችሮታው ሰፊ ጥበበኛ ነው። » አል ኒሳእ 130

ሁሉም ነገር አስተዳደርና መሪ እንዳለው ሁሉ ትዳርም ብቁ መሪና የሰከነ አስተዳዳሪ ይፈልጋል።

በጣም ጥቃቅን ፍሞችን ከባሎች የአያያዝና የማብረድ ጉድለት የተነሳ በእንስቶቹ እጅ ሲነድ ታየዋለህ።

ወንዶች ዘንድ ተወቃሿ ፣ ተተቺዋና ድሮም እናንተ እየተባለ የሚተረተው በሚስቶች ሲሆንም ትሰማለህ።

በዚያው ልክ ሴቶች ዘንድም ጠቅለል ተደርጎ " ወንዶች ስትባሉ እንደው… … " እየተባለ ሲወገዝ ትሰማለህ።

ይኸ ጥቅል ወቀሳ ግን አጥፊዎችን ከመሸሸግ ውጪ ምንም ጥቅም የለውም።

ይልቅ ከምርጫ ጀምሮ ራስህን አበጅተህና አውቀህ ከገባህበት፤ ከዚያም የሚነሱ አለመግባባቶችን በትእግስት መፍታት ከቻልክ ቤትህ የዱንያ ጀነት አርፎበታልና ምቾታችሁ፣ ድሎታችሁና ደስታችሁ ሁሌም የሚረሳ አይሆንም።

እርግጥ ነው አንተም ሰው ነህና ድክመትም ስህተትም አይለይህም። እንዴት ቤትህን በስርኣት ማስተዳደር ያቅተሃልም አይባልም።

ነገር ግን ሃላፊነትህን ለመወጣት ንቁ ተሳትፎ ካደረክ በአላህ ፈቃድ ብዙዎቹን የትዳርህን ቁስሎች ማከም ትችላለህ።

ለዚህ ብቃትህ ወሳኙ ቁልፍ ደግሞ የአጋርህን ግንዛቤ፣ ባህሪ፣ ፍላጎትና ስሜት እንዲሁም አቅም ማወቅ ነው። ከዚያም ተመጣጣኝ ምላሽ መስጠትህ ነው።

የዚያን ግዜ ድክመታችሁ ማሳበቢያ ስለማይኖረው የግድ ራሳችሁን ለማረም ደፋቀና ትላላችሁ።

ያለዚያ እያለቀስክ ወይም እያስለቀስክ በሁለት በደሎች መሃል መኖር ሊከሰትብህ ይችላል።

መከላከል እየቻሉ ራስን ለጉዳት መዳረግም ሆነ፤ ሌሎችን የሚጎዳ ነገር ማድረግ ደግሞ በነቢያችን ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም አንደበት የተኮነነ ጉዳይ ነው።

قال النبي صلى الله عليه وسلم : (لَا ضَرَرَ وَلَا ضِرَارَ) أخرجه أحمد (2865) وابن ماجه (2341) وصححه الألباني في صحيح ابن ماجه

«(በሸሪዓ) ጉዳትም መጎዳዳትም የለም! » አልሀዲስ

قال رسول الله صلى الله عليه وسلم : ( اتقوا الظلم، فإن الظلم ظلمات يوم القيامة ) رواه مسلم

«በደልን ተጠንቀቁ! የትንሳዔው እለት በደል ጨለማዎች ናትና» ሙስሊም ዘግበውታል

አንተም አትበድል! እንዲበድሉህም አትመቻች!

አላህ የተሳካላቸው ባለ ትዳሮች ያድርገን!!

በደል ከማድረስም ፣ ተበዳይ ከመሆንም ይጠብቀን!!

አሚን!!

የትዳር ውስጥ ችግሮችን መፍታት በተመለከተ ከባልም ይሁን ከሚስት ምን ምን አስተዋፅኦ ይጠበቃል 

والله أعلم، وصلى الله على نبينا محمد وعلى آله وصحبه وسلم تسليما كثيرا.

ke 

yetewesede