Thursday, August 4, 2016

1ኛ ሓዲስ - አርበዒን።

📚📚📚

بسم الله الرحمن الرحيم

الحديث الأول

" إنما الأعمال بالنيات "

عَنْ أَمِيرِ الْمُؤْمِنِينَ أَبِي حَفْصٍ عُمَرَ بْنِ الْخَطَّابِ ( قَالَ: سَمِعْت رَسُولَ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم يَقُولُ: " إنَّمَا الْأَعْمَالُ بِالنِّيَّاتِ، وَإِنَّمَا لِكُلِّ امْرِئٍ مَا نَوَى، فَمَنْ كَانَتْ هِجْرَتُهُ إلَى اللَّهِ وَرَسُولِهِ فَهِجْرَتُهُ إلَى اللَّهِ وَرَسُولِهِ، وَمَنْ كَانَتْ هِجْرَتُهُ لِدُنْيَا يُصِيبُهَا أَوْ امْرَأَةٍ يَنْكِحُهَا فَهِجْرَتُهُ إلَى مَا هَاجَرَ إلَيْهِ".

رَوَاهُ إِمَامَا الْمُحَدِّثِينَ أَبُو عَبْدِ اللهِ مُحَمَّدُ بنُ إِسْمَاعِيل بن إِبْرَاهِيم بن الْمُغِيرَة بن بَرْدِزبَه الْبُخَارِيُّ الْجُعْفِيُّ [رقم:1]، وَأَبُو الْحُسَيْنِ مُسْلِمٌ بنُ الْحَجَّاج بن مُسْلِم الْقُشَيْرِيُّ النَّيْسَابُورِيُّ
[رقم:1907] رَضِيَ اللهُ عَنْهُمَا فِي "صَحِيحَيْهِمَا" اللذِينِ هُمَا أَصَحُّ الْكُتُبِ الْمُصَنَّفَةِ.

🇸🇦🇸🇦🇸🇦🇸🇦🇸🇦
1⃣ 1ኛ  ሓዲስ

🔴 የሓዲሱ ትርጉም

⭕ ስራዎች ሁሉ የሚመዘኑት በንያ (ባሰብከው ሃሳብ) ነው።
ሁሉም ሰው (የነየተው ነገር) ያሰበው ነገር አለው።

📖 የሙእሚኖች መሪ የሆነው ዑመር ኢብኒ ኸጣብ የአላህ መልእክተኛ صلى الله عليه وسلمእንዲህ ሲሉ ሰምቻቸዋሎህ አለ። “ስራዎች ሁሉ የሚመዘኑት በንያ (ባሰብከው ሃሳብ) ነው። ሁሉም ሰው (የነየተው ነገር) ያሰበው ነገር አለው። ሰው ሁሉ ደግሞ (የነየተውን) ያሰበውን ያገኛል። ስደቱ ወደ አላህ እና ወደ መልእክተኛው ከሆነ፥ ስደቱ ወደ አላህ እና ወደ መልእክተኛው ይሆንለታል። ስደቱ ደግሞ ሊያገኛት ወደሚፈሊጋት አለም  (ዱንያ) ወይንም ሊያገባት ወደሚፈልጋት ሴት ከሆነ፥ ስደቱ ወደተሰደተለት ምክንያት ይሆንለታል”

📖 ሓዲሱን ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል።

♨ ከአንደኛው ሓዲስ የምንወስዳቸው ትምህርቶች

🔰 ሁሉም ስራ ንያ እንዳለው።
🔰 ሁሉም ሰው በንያው መሰረት ስራው እንደሚመዘንለት።
🔰 የሚያስተምር ሰው ምሳሌን እያጠቀሰ ቢያስተምር ጥሩ እንደሆነ።

በ ዓብዱሰመድ መሐመድኑር

➖➖➖

Monday, July 18, 2016

" ስንቅና ሰናቂው"


🔘🔘🔘

" ስንቅና ሰናቂው"

ይቅርና መቶ — ደሞ ሁለት መቶ
አስር ሃያ ሚሊዮን—ሲባል ጆሮ ሰምቶ
ገርሞኝ ያስቀኛል —ቁጥሩ በ‘ጅግ በዝቶ
አስደንጋጩ አሃዝ —ለልቤ ተንዛዝቶ።

ናፍቆኝም አይደለ— ሆኖም አይደል ህልሜ
ሲጠራ ስሰማ— እንዲህ መደመሜ
ልፋቱ ገርሞኝ ነው —ሳይታክት መድከሙ
ዱንያን ለመሰብሰብ— እንዲህ መፋለሙ
ቀን ተሌት ሳይሰንፍ —አጥብቆ ማለሙ።
 ለዚህ ለጠፊ አለም— እንዲህ የታጠቀ
ለቀብሩም አስቦ —ስንቁን ከሰነቀ
ጀግንነት ነው መቸም —ብርቱ ጥንካሬ
እንዲህ ወንድም ሲገኝ —ባገር በመንደሬ።
ሸቀጡን ሲቃርም— እረፍት እየነሳው
ልቡን አስክሮለት— ቀብሩን ካረሳሳው
ይሄ ነው ደካማ— የንዋይ አምላኪ
የዱንያ ምርኮኛ —የሸቀጥ ሰባኪ!

በ ኡስታዝ መሐመድ ሲራጅ

➖➖➖

Friday, April 1, 2016

አንድ ባል የወር አበባ ደም ላይ ካለች ሚስቱ ጋር ግንኙነት መፈፀም እንደማይችል የምናውቀው ስንቶቻችን እንሆን? ጥፋቱስ ከተፈፀመ ማካካሻው ምንድን ነው?

(ኢብኑ ሙነወር፣ ነሐሴ 15/2007)

አንድ ባል የወር አበባ ደም ላይ ካለች ሚስቱ ጋር ግንኙነት መፈፀም እንደማይችል የምናውቀው ስንቶቻችን እንሆን? ጥፋቱስ ከተፈፀመ ማካካሻው ምንድን ነው?

1. ብይኑ
በወር አበባ ወቅት የግብረ-ስጋ ግንኙነት መፈፀም በጥብቅ የተከለከለ አደገኛ ወንጀል ነው፡፡ ጌታችን አላህ እንዲህ ይላል፡-
وَيَسْأَلُونَكَ عَنِ الْمَحِيضِ قُلْ هُوَ أَذًى فَاعْتَزِلُوا النِّسَاءَ فِي الْمَحِيضِ وَلَا تَقْرَبُوهُنَّ حَتَّى يَطْهُرْنَ فَإِذَا تَطَهَّرْنَ فَأْتُوهُنَّ مِنْ حَيْثُ أَمَرَكُمُ اللَّهُ إِنَّ اللَّهَ يُحِبُّ التَّوَّابِينَ وَيُحِبُّ الْمُتَطَهِّرِينَ (222)
“ስለ የወር አበባ ደም ይጠይቁሃል፡፡ ‘እርሱ አስፀያፊ ነገር ነው፡፡ ስለሆነም ሴቶችን በወር አበባ ጊዜ (ከመገናኘት) ራቋቸው፡፡ ንፁህ እስከሚሆኑም ድረስ አትቅረቧቸው፡፡ ንፁህ በሆኑም ጊዜ አላህ ካዘዛችሁ ስፍራ ተገናኟቸው፡፡ አላህ ተመላሾችን ይወዳል፤ ተጥራሪዎችንም ይወዳል’ በላቸው፡፡” [አልበቀራህ፡ 222]
ነብዩም ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም፡- “የወር አበባ ደም ላይ ያለችን ሴት የተገናኘ ወይም ሴትን በፊንጢጣዋ የተገናኘ ወይም ከጠንቋይ ዘንድ የሄደ ሰው በሙሐመድ ላይ በወረደው ክዷል” ይላሉ፡፡ ሐዲሡን አልባኒ “ሶሒሕ” ብለውታል፡፡ [ሶሒሑትተርጊብ ወትተርሂብ፡ 2433]
2. በወር አበባ ጊዜ ግንኙነት ከተፈፀመ የጥፋቱ ማካካሻው ምንድን ነው?
በዚህ ግንኙነት በማይፈቀድበት ወቅት ላይ ግንኙነት የፈፀመ ሰው ከባድ ጥፋት ፈፅሟል፡፡ ለጥፋቱ ማበሻ ይሆነውም ዘንድ አንድ ዲናር ወይም ግማሽ ዲናር ሊመፀውት እንደሚገባ ነብያችን ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ደንግገዋል፡፡ [ሶሒሕ አቢ ዳውድ፡ 257] አንድ ዲናር ማለት 4.25 ግራም ወርቅ ሲሆን ግማሹ ደግሞ 2.125 ግራም ነው፡፡ እናም በዚህ ጊዜ ግብረ-ስጋ ግንኙነት የፈፀመ ሰው ይህን ያክል ይሰድቃል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የዘመኑ የአንድ ግራም ወርቅ ዋጋ ለምሳሌ 800 ብር ቢሆን 4.25 x 800= 3,400 ብር ወይም ደግሞ የዚህን ግማሽ 2.125 x 800=1,700 ብር ሊሰድቅ ይገባል ማለት ነው፡፡
እንግዲህ ተመልከቱ አንድ ሰው አንዴ ለፈፀመው ህገ-ወጥ ግንኙነት ቅጣት ይሆን ዘንድ ይህን ያክል ገንዘብ አንዴ ባግባቡ ቢያወጣ ዳግም ወደዚህ ጥፋት የመመለስ እድሉ በጅጉ ይጠብ ነበር፡፡ ነገር ግን ህጉን ባለማወቃችን ወይም ደግሞ የጥፋቱን ክብደትና ማካካሻውን ጠንቅቀን ባለመረዳታችን ምክንያት ስንቶቻችን ነን በወንጀል የምንጨማለቀው?! አላህ ድንጋጌዎቹን የምንረዳ ለህጉ የምናድር ያድርገን፡፡
ሸይኹልአልባኒ ረሒመሁላህ እንዲህ ይላሉ፡ “ነፍሱ አሸንፋው የወር አበባ ላይ ያለችን ሴት ከደሟ ከመጥራቷ በፊት የተገናኘ ሰው በሱ ላይ አቅራብ በሆነ ስሌት ግማሽ የእንግሊዝ ፓውንድ ወርቅ ወይም እሩቡን የመመፅወት ግዴታ አለበት፡፡ ይህም ዐብዱላህ ኢብኒ ዐባስ ከነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ያስተላለፈውን የወር አበባ ላይ ሳለች ሚስቱን ስለሚገናኝ ሰው “በአንድ ዲናር ወይም በግማሽ ዲናር ይሰድቅ” ሲሉ የተናገሩትን ሐዲሥ መነሻ በማድረግ ነው፡፡ … ምናልባትም በአንድ ዲናር ወይም በግማሹ ተብሎ አማራጭ መሰጠቱ ወደ መፅዋቹ የአቅም ሁኔታ የሚመለስ ሊሆን ይችላል፡፡ ምንም እንኳን ሰነዳቸው ደካማ ቢሆንም የሐዲሡ አንዳንድ ዘገባዎች ይህን ያመላክታሉ፣ ወላሁ አዕለም፡፡” [አዳቡዝዚፋፍ፡ 50]
3. ግን ለምን በወር አበባ ጊዜ ግነኙነት ተከለከለ?
በዚህ ሰአት ግንኙነት መፈፀሙ አስፀያፊ መሆኑ ህሊናው ላልታወረ ሁሉ አይሰወርም፡፡ ከዚያም ባለፈ የራሱ የሆነ ጉዳት አለው፡፡ ደረጃው ቢለያይም ለወንዱም ለሴቷም የጎንዮሽ ጉዳት እንዳለው ምሁራን ይገልፃሉ፡፡ ብዙ ሴቶች የወር አበባ ላይ ሲሆኑ ለአእምሮ አለመረጋጋት፣ ብስጭት፣ ድብርት፣ የጀርባ ህመም፣ የሆድ ቁርጠት፣ ማቅለሽለሽ፣ ድካም፣ ራስ ምታትና መሰል ህመሞች ያጋጥሟቸዋል፡፡ የእለት ከእለት ስራዎቻቸውን ለማከናወን የሚያቅታቸው ሁሉ አሉ፡፡ እናም የወር አበባ ኡደታዊ ደም ወቅታዊ ቢሆኑም የተለያዩ ማህበራዊና ስነ ልቦናዊ ጫናዎችን ያሳድራል፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ ግንኙነት መፈፀም በተለይም ሴቷ ላይ ይበልጥ ችግር መፍጠር፣ ይበልጥ ስቃይን መጨመር ነው፡፡ በዚያ ላይ ማህፀን አካባቢ እራሱን የቻለ የህመም ስሜት አለ፡፡ በዚህ ሰአት ማህፀንና አካባቢው ከወትሮው በተለየ መልኩ የመኮማተርና የመድከም ባህሪ ስለሚኖረው ባእድና ውጫዊ አካል ካገኘው የመቁሰል፣ በኢንፌክሽን የመጠቃት፣ ለተጨማሪ ህመም የመጋለጥ እድሉ ሰፊ ነው፡፡
4. በወር አበባ ወቅት ባል ከሚስቱ የሚፈቀድለት ምንድን ነው?
በወር አበባ ወቅት የሩካቤ ስጋ ግንኙነት እንጂ አብሮ መብላት፣ መጠጣት፣ መቀመጥ አልተከለከለም፡፡ ኢስላም በዚህ ረገድ የተለየ ህግ አለው፡፡ በክርስትና በወር አበባ ወቅት ሴቷ እሷ ብቻ ሳትሆን የነካትም ጭምር የረከሰ ነው፡፡ "ሴት ጊዜዉን እየጠበቀ የሚመጣ የደም መፍሰስ ቢኖርባት የወር አበባዋን ርኩሰት እስከ ሰባት ቀን ይቆያል፡፡ #በዚህ_ጊዜ #ማንም_ሰዉ_ቢነካት እስከ ማታ ድረስ #እርኩስ ይሆናል፡፡ በወር አበባዋ ጊዜ #የምትተኛበት_ነገር #ማንኛዉም_ነገር_እርኩስ_ይሆናል፡፡ #የተቀመጠችበትን_ማንኛዉም ነገር #የነካ_ሰዉ ልብሱን ይጠብ ሰዉነቱንም ይታጠብ #እስከ_ማታ_ድረስ_ግን #እርኩስ_ይሆናል" ይላል መፅሀፋቸው፡፡ [ዘሌዋዉያን 15: 19-22] አይሁዶችም ዘንድ ያለው ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ አነስ ኢብኑ ማሊክ ረዲየላሁ ዐንሁ እንዲህ ይላሉ፡ “የሁዶች ከነሱ አንዲት ሴት የወር አበባ ካየች ከቤት ያስወጧት ነበር፡፡ አብረዋት አይበሉም፣ አብረዋትም አይጠጡም፣ በቤቶቻቸውም ውስጥ አብረዋት አይቀላቀሉም ነበር፡፡ የአላህ መልእክተኛ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ስለዚህ ሲጠየቁ የጠራው አላህ ‘ስለ የወር አበባ ደም ይጠይቁሃል፡፡ እርሱ አስፀያፊ ነገር ነው፡፡ ስለሆነም ሴቶችን በወር አበባ ጊዜ (ከመገናኘት) ራቋቸው’ የሚለውን እስከመጨረሻው አወረደ፡፡ የአላህ መልእክተኛም ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ‘በቤቶቻችሁ ውስጥ ተቀላቀሏቸው፡፡ የሩካቤ ስጋ ግንኙነት ሲቀር ሁሉንም ነገር ፈፅሙ’ አሉ፡፡ የሁዶች ይህ ነገር ሲደርሳቸው ‘ይሄ ሰውየ ከኛ ጉዳይ ውስጥ የሚፃረር ቢሆን እንጂ አንድም ነገር አልቀረውም!!’ አሉ፡፡...” [ሶሒሕ አቢ ዳውድ]
ስለዚህ ሸሪዐችን በወር አበባ ወቅት ሴቶችን በምግብ፣ በመኝታና መሰል ነገሮች ማግለልን አያስተምርም፡፡ ደሙ በራሱ ቆሻሻ ቢሆንም ከዚያ ባለፈ ሌሎች ዘንድ እንደሚስተዋለው መላ አካሏን የነካትን ነገር ሁሉ የረከሰ ነው አንልም፡፡ ያሳለፍነው ማስረጃ በቂ ቢሆንም ለማጠናከር ያክል ጥቂት እንጨምር
- በአንድ ወቅት ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ዓኢሻ ሆይ! እሱን ልብስ አቀብይኝ” ሲሏት “የወር አበባ ላይ ነኝ” አለቻቸው፡፡ ይህኔ እሳቸው “የወር አበባሽ ከእጅሽ ላይ አይደለም” አሏት፡፡ [ሙስሊም] መይሙናም ረዲየላሁ ዐንሃ ባለቤቷ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የወር አበባ ላይ እያለች አብረዋት ይተኙ እንደነበር ገልፃለች፡፡ [ሙስሊም] ኡሙ ሰለማህ ባስተላለፈችው ደግሞ “በአንድ ወቅት ከአላህ መልእክተኛ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ጋር ጋቢ ለብሼ ተኝቼ ሳለሁ የወር አበባየ መጣብኝና ቀስ ብየ ወጣሁኝና የወር አበባ ልብሴን ያዝኩኝ፡፡ የአላህ መልእክተኛ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ‘የወር አበባሽ መጣ?’ አሉኝ፡፡ ‘አዎ’ አልኳቸው፡፡ ከዚያም ጠሩኝና በጋቢው ውስጥ አብሬያቸው ተኛሁኝ፡፡” [ቡኻሪና ሙስሊም]
- እናታችን ዓኢሻ ረዲየላሁ ዐንሃ “የወር አበባ ላይ ሆኜ የአላህ መልእክተኛን ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እራሳቸውን አጥብ ነበር”፣ “ፀጉራቸውን አበጥር ነበር” ትላለች፡፡ [ቡኻሪና ሙስሊም]፣ [ቡኻሪ]
- ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የወር አበባ ላይ ካለች ሚስታቸው ጋር አብረው ይበሉና ይጠጡ ነበር፣ ኧረ እንዳውም ከዚያም በላይ!! ዓኢሻህ ረዲየላሁ ዐንሃ እንዲህ ትላለች “የወር አበባ ላይ እያለሁ እጠጣና ከዚያም ለነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም (መጠጫውን) አቀብላቸው ነበር፡፡ እሳቸውም አፋቸውን አፌን ካሳረፍኩበት ቦታ ላይ አድርገው ይጠጡ ነበር፡፡ የወር አበባ ላይ ሆኜ አጥንት እግጥና ከዚያም ለነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም አቀብላቸዋለሁ፡፡ እሳቸውም አፋቸውን አፌ ካረፈበት ቦታ ያደርጉ ነበር፡፡” [ሙስሊም]
- እንዳውም የወር አበባ ላይ ካለች ሚስታቸው እቅፍ ስር ሆነው የተከበረውን ቁርኣን ያነቡ ነበር፡፡ እናታችን ዓኢሻህ እንዲህ ትላለች፡- “(ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እኔ የወር አበባ ላይ ሆኜ ከእቅፌ ውስጥ ይደገፉ ነበር፡፡ ከዚያም ቁርኣን ይቀሩ ነበር፡፡” [ቡኻሪና ሙስሊም] “ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እኔ የወር አበባ ላይ እያለሁ ከጎናቸው ተኝቼ ይሰግዱ ነበር፡፡ ሱጁድ ሲወርዱ ልብሳቸው ይነካኝ ነበር” ትላለች፡፡ [ቡኻሪ]
- ባጭሩ ከላይ እንዳሳለፍነው ከግብረ-ስጋ ግንኙነት ውጭ ሁሉም ነገር ይፈቀዳል፡፡ እናም ብልት በሚገባ ከተሸፈነ ያሰኘውን ከሚስቱ ጋር መጫወትና መጣቀም ይችላል ማለት ነው፡፡ ኢብኑ ቁዳማህ ረሒመሁላህ “የደሙ ቦታ በክልከላ መለየቱ ከሱ ውጭ ባሉት የተፈቀደ መሆኑን ጠቋሚ ነው” ይላሉ፡፡ [አልሙግኒ፡ 1/415] ይህ ማለት ግን በፊንጢጣ ግንኙነት መፈፀም ይፈቀዳል ማለት አይደለም፣ ነዑዙቢላህ! ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ሴትን በፊንጢጣዋ የተገናኘ የተረገመ ነው!” ብለዋልና፡፡ [ሱነን አቢ ዳውድ፡ 2162] በተጨማሪም “…ሴትን በፊንጢጣዋ የተገናኘ ወይም ከጠንቋይ ዘንድ የሄደ ሰው በሙሐመድ ላይ በወረደው ክዷል” ብለዋልና፡፡ [ሶሒሑትተርጊብ ወትተርሂብ፡ 2433]
ማሳሰቢያ፡-
የወር አበባን የሚመለከተው ብይን የወሊድ ደምንም በተመሳሳይ ይመለከታል፡፡ ኢብኑ ቁዳማህ ረሒመሁላህ “የወሊድ ደም ላይ ያሉም ልክ የወር አበባ ላይ እንዳለችዋ ነው የሚታዩት በዚህ ረገድ” ይላሉ፡፡ [አልሙግኒ፡ 1/419] ወላሁ አዕለም፡፡ ሼር ማድረግ አይርሱ፡፡ ሌሎችን ከጥፋት ይታደጉ፡፡

(ኢብኑ ሙነወር፣ ነሐሴ 15/2007)

Tuesday, March 15, 2016

9ኛ ሓዲስ:በአቅማችን ልክ እንደታዘዝን እና ልዩነትን ከማምጣት እንደተከለከልን።

الحديث التاسع

التكليف بما يستطاع والنهي عن الاختلاف

عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ عَبْدِ الرَّحْمَنِ بْنِ صَخْرٍ  قَالَ: سَمِعْت رَسُولَ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم يَقُولُ: "مَا نَهَيْتُكُمْ عَنْهُ فَاجْتَنِبُوهُ، وَمَا أَمَرْتُكُمْ بِهِ فَأْتُوا مِنْهُ مَا اسْتَطَعْتُمْ، فَإِنَّمَا أَهْلَكَ الَّذِينَ مِنْ قَبْلِكُمْ كَثْرَةُ مَسَائِلِهِمْ وَاخْتِلَافُهُمْ عَلَى أَنْبِيَائِهِمْ ".
رَوَاهُ الْبُخَارِيُّ [رقم:7288]، وَمُسْلِمٌ [رقم:1337].

9ኛ  ሓዲስ

የሓዲሱ ትርጉም

በአቅማችን ልክ እንደታዘዝን እና ልዩነትን ከማምጣት እንደተከለከልን።

አቡ ሁረይራ  የአላህ መልእክተኛ صلى الله عليه وسلمእንዲህ ሲሉ ሰምቻቸዋሎህ አለ። “ የከለከልኳቹሁን ሁሉ ተከልከሉ። ካዘዝኳቹህ ውስጥ ደግሞ የቻላችሁትን ስሩ። ከናንተ በፊት የነበሩትን ህዝቦች ያጠፋቸውኮ ጥያቄ ማብዛታቸው እና ከብዮቻቸው መለያየታቸው ነው።”
ሓዲሱን ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል።

ከዘጠነኛው ሓዲስ የምንወስዳቸው ትምህርቶች

1. በቁርንአን እና በሓዲስ ከተከለከልነው ነገር መራቅ እንዳለብን።
2. በቁርአን እና በሓዲስ የታዘዝነውን ነገር የቻልነውን ያክል መስራት እንዳለብን።
3. ዲናችን(ሃይማኖታችን) ከአቅማችን በላይ የሆነን ነገር(የማንችለውን) እንድንሰራ እንደማያስገድደን።
4. የሚያስፈልገውን ጥያቄ ብቻ መጠየቅ እና ዝምብለን ጥያቄ ማብዛት እንደሌለብን(በተለይ ደግሞ በዋሒ ግዜ)።
5. ነብያት ላይ ጥያቄ ማብዛት እና ካመጡት ነገር መለየት(አለመከተል) ጥመትን እና ጥፋትን እንደሚያመጣ።

Saturday, February 6, 2016

የቁርኣን ሰዎች

ከ ወንድም Ibnu Munewor የተወሰደ።

ሸይኽ ሳሊሕ አልፈውዛን እንዲህ ይላሉ: "የቁርኣን ሰዎች ሲባል የሚፈለገው የሚያፍዙት፣ በሥርዓት የሚያነቡት ወዘተ ••• ማለት አይደለም። የቁርኣን ሰዎች የሚባሉት ባያፍዙት እንኳን የሚሰሩበት ናቸው። እነዚያ ትእዛዛቱን የሚፈፅሙ፣ ክልከከላውን የሚርቁ፣ ከወሰኑ የሚቆሙ እነሱ ናቸው የቁርኣን ሰዎች። እነዚህ የአላህ ሰዎች ናቸው፣ ከፍጡሩ ልዩዎቹ! ቁርኣንን አፍዞ፣ አሳምሮ የሚቀራና ሑሩፎቹን አስተካክሎ እያነበበ ነገርግን ድንጋጌዎችቹን የሚጥስ የሆነ ሰው ይሄ የቁርኣን ሰው አይደለም። ከአላህ ልዩ ሰዎች ውስጥም አይደለም። ይልቁንም ይሄ አላህና መልእክተኛውን የሚያምፅ ቁርኣንንም የሚፃረር ነው። አዎ።
የቁርኣን ሰዎች በተጨማሪ እነዚያ ማስረጃ የሚያደርጉት ናቸው። በማስረጃ አጠቃቀም ላይ በሱ ላይ ሌላን የማያስቀድሙ ናቸው። ፊቅሁንም አሕካሙንም በጥቅሉ ዲናቸውንም ከሱ ይወስዳሉ። እነዚህ ናቸው የቁርኣን ሰዎች።
【ሸርሑ ኪታቢ አልዑቡዲያህ】

ከ ወንድም Ibnu Munewor የተወሰደ።

Thursday, December 24, 2015

ያስፈልገዎታል!! ጀናባን የሚመለከቱ ህግና ደንቦች።

ከወንድም ኢብኑ ሙነወር የተወሰደ።

ያስፈልገዎታል!!
                         ጀናባን የሚመለከቱ ህግና ደንቦች

የቃላት መፍቻ፡-

1.   መኒይ (የዘር ፈሳሽ)፡-

- በስሜት ተስፈንጥሮ ከእርካታ ጋር የሚወጣ ፈሳሽ ነው፡፡
- ለወንድ ወፍራምና (ወደ ቢጫነት የሚያደላ) ነጭ ፈሳሽ ሲሆን ለሴት ደግሞ ቀጭንና ቢጫ ነው፡፡ [ሙስሊም፡ 311] ሽታው ወደሊጥ ሽታ የቀረበ ነው፡፡ በሆነ ምክንያት እነዚህ መታወቂያዎች ሊቀየሩ ይችላሉ፡፡
- ከወጣ በኋላ የሰውነት መቀዝቀዝ ዘና ማለት (ፉቱር) ይከተላል፡፡
- ፈሳሹ ሚዛን በሚደፋው የዑለማእ እይታ ጦሀራ እንጂ ነጃሳ አይደለም፡፡ ይህን የሚደግፉ ሶሒሕ ማስረጃዎች መጥተዋል፡፡ [ሙስሊም፡ 694] [አልኢርዋእ፡ 1/197]
- በውንም ይሁን በህልም ከወጣ ገላን መታጠብ ግዴታ ነው፡፡

2.   መዚይ፡-

- ግንኙነትን ሲታሰብ ወይም ሲፈለግ የሚወጣ ያዝ የሚያደርግ (የሚያጣብቅ)፣ ቀለም አልባ ቀጭን ፈሳሽ ነው፡፡
- አወጣጡ ከእርካታ ጋር አይደለም፡፡ ተስፈንጥሮ ስለማይወጣ መውጣቱ ላይስተዋል ይችላል፡፡
- ነጃሳ ስለሆነ የነካውን አካል ማጠብ ይገባል፡፡ ልብስን ግን የነካው ቦታ ላይ ውሃ በመርጨት ማፅዳት በቂ ነው፡፡
- የነካውን ቦታ እንጂ ገላን መታጠብ ግን ግዴታ አይደለም፡፡ ውዱእን ግን ያፈርሳል፡፡

3.   ወዲይ፡-

- ከሽንት በኋላ የሚወጣ ነጭ ሽታ አልባ ፈሳሽ ነው፡፡
- የሚያጣብቅ አይደለም፡፡
- ብይኑ ከሽንት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

4.   ከሴቶች ብልት የሚወጣ ፈሳሽ፡-

- ከማህፀን የሚወጣ ቀጭን ፈሳሽ ነው፡፡ መጠኑ ከሴት ሴት ይለያያል፡፡
- ሴቷ መውጣቱንም ላታስተውለው ትችላለች፡፡
- አካልንም ልብስንም ቢነካ አይነጅስም፣ ጦሃራ ነው፡፡
- ውዱእን ግን ያፈርሳል፡፡ ከሁለቱም መፀዳጃዎች በኩል የሚወጣ ነገር ውዱእ ያፈርሳልና፡፡ አወጣጡ ቋሚ ከሆነ ግን ለያንዳንዱ ሶላት ወቅቱ ከገባ በኋላ ውዱእ እያደረገች መስገድ ይገባል፡፡ ውዱእ ካደረገች በኋላ ቢወጣ ቦታም አይሰጠውም፡፡

                      ገላን መታጠብ ግዴታ የሚሆነው መቼ ነው?

1. በውኑ ግንኙነት ከተፈፀመ የዘር ፈሳሽ (መኒይ) #ቢፈስም_ባይፈስም ትጥበት ግዴታ ነው፡፡
2. ግንኙነት #ባይፈፀምም የዘር ፈሳሽ (መኒይ) #ከእርካታ ጋር ከወጣ ትጥበት ግዴታ ነው፡፡
3. በህልሙ ግንኙነት እንደፈፀመ አይቶ የዘር ፈሳሽ (መኒይ) ካገኘ በማያሻማ መልኩ መታጠብ ግዴታ ነው፡፡
4. በህልሙ ግንኙነት እንደፈፀመ አይቶ ነገር ግን ሲነቃ ምንም አይነት የዘር ፈሳሽ (መኒይ) ካላገኘ በማያሻማ መልኩ የመታጠብ ግዴታ የለበትም፡፡ ኡሙ ሱለይም የተባለችዋ ሶሐቢያህ ረዲየላሁ ዐንሃ “የአላህ መልእክተኛ ሆይ! አንዲት ሴት ኢሕቲላም ከሆነች (በህልሟ ግንኙነት ስትፈፅም ካየች) የመታጠብ ግዴታ አለባትን?” ብላ ስትጠይቅ “ፈሳሽ ካየች አዎ” ሲሉ መልሰውላታል፡፡ [ቡኻሪና ሙስሊም]
5. በህልሙ ግንኙነት ሲፈፅም አላየም ወይም አያስታውስም፡፡ ነገር ግን ሲነቃ የዘር ፈሳሽ (መኒይ) ካገኘ በማያሻማ መልኩ የመታጠብ ግዴታ አለበት፡፡
6. በህልሙ ግንኙነት ሲፈፅም አላየም ወይም አያስታውስም፡፡ ነገር ግን ሲነቃ ፈሳሽ አገኘ፡፡ የዘር ፈሳሽ (መኒይ) እንዳልሆነ እርግጠኛ ከሆነ የመታጠብ ግዴታ የለበትም፡፡ የነካውን ግን ሊያጥብ ይገባል፡፡ ብይኑ የሽንት ብይን ነውና፡፡
7. በህልሙ ግንኙነት ሲፈፅም አላየም ወይም አያስታውስም፡፡ ነገር ግን ሲነቃ የዘር ፈሳሽ (መኒይ) ይሁን አይሁን #መለየት_ያልቻለው ፈሳሽ ካገኘ በ ሽታ ወይም በቻለው መንገድ ለመለየት ይሞክርና ጥርጣሬው መኒይ ወደመሆኑ ካደላ ይታጠብ፡፡ ጥርጣሬው መዚይ ወደመሆኑ ካደላ ግን በተለይም ከመተኛቱ በፊት ስለ ግንኙነት አስቦ ከነበር እንደ መዚይ ይቁጠረውና የነካውን ቦታ ብቻ ይጠብ፡፡ ገላውን የመታጠብ ግዴታ የለበትም፡፡ ቢታጠብ ከጥንቃቄ አንፃር የተሻለ ነው፡፡
8. በህልሙ ግንኙነት ሲፈፅም አላየም ወይም አያስታውስም፡፡ ነገር ግን ሲነቃ የዘር ፈሳሽ (መኒይ) ይሁን አይሁን #መለየት_ያልቻለው ፈሳሽ ካገኘና ግምቱ ወደየትኛውም ካላደላ፣ ከመተኛቱ በፊት ስለ ግንኙነት #ያላሰበ ከሆነ ጉዳዩ አወዛጋቢ ቢሆንም ትክክለኛው ትጥበት የለበትም የሚል ነው፡፡ ቢታጠብ ከጥንቃቄ አንፃር የተሻለ ነው፡፡ [ፈታዋ ኢብኑልዑሠይሚን፡ 11/161]

የጀናባ አስተጣጠብ ሁለት አይነት ነው፡፡

1. የሚያብቃቃ ማለትም ግዴታውን ለማውረድ የሚጠበቅ ሲሆን እሱም ሙሉ አካልን በውሃ ማዳረስ ነው፡፡ ባይሆን መጉመጥመጥና በአፍንጫ ውሃ መሳብ (ኢስቲንሻቅ) እንዳይረስ፡፡ ለትጥበት ኒያ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ አንድ ሰው ጀናባ ማውረድን ሳያስብ እንዲሁ ውሃ ውስጥ ዋኝቶ ቢወጣ መላ አካላቱ ውሃ መንካቱ ብቻ ጀናባው ለመውረዱ በቂ አይሆንም፡፡ ይስተዋል! ይህን ትጥበት ካደረጉ በኋላ ውዱእም ባያደርጉ መስገድ ይቻላል፡፡ ባይሆን ከትጥበቱ መሀል ውዱእ የሚያፈርስ ነገር መፈፀም የለበትም፡፡
2. ሌላኛውና በላጩ ግን በቅድሚያ ሁለት እጆችን መታጠብ፡፡ ከዚያም ኢስቲንጃእ ማድረግ፡፡ ከዚያም ውዱእ ማድረግ፡፡ ከዚያም ከእራስ ጀምሮ ቀሪ አካላትን ውሃ ማዳረስ፡፡ እግርን ከውዱእ ጋር ማጠብም ይቻላል፤ መጨረሻ ላይ ማጠብም ይቻላል፡፡ [ቡኻሪና ሙስሊም]

ማሳሰቢያ፡-

ሴቷ ለትጥበት ስትል የፀጉር ጉንጉኗን የመፍታት ግዴታ የለባትም፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም: ኡሙ ሰለማህ ለጀናባህ ወይም ለሐይድ ትጥበት ፀጉሯን “ልፍታው ወይ?” ብላ ስትጠይቃቸው “አይ! የሚበቃሽ ከእራስሽ ላይ ሶስት ጊዜ ውሃ ማፍሰስ ብቻ ነው” ብለዋታል፡፡ [ሙስሊም] ስለዚህ ፀጉር ሳይፈታ ውሃ መድረስ ከቻለ መፍታት አይጠበቅም፡፡

ለማጣቀሻነት የተጠቀምኩት
1. ፈታዋ ኢብኑልዑሠይሚን
2. ፈትሑልዐላም ፊ ዲራሰቲ አሓዲሢ ቡሉጊልመራም እና ሌሎችም
ሼር ማድረግ እንዳይረሱ፡፡

(ኢብኑ ሙነወር፣ ህዳር 8/2008)

Friday, November 27, 2015

ኔትዎርክ ማርኬቲንግ በሸሪዓ እይታ



ኔትዎርክ ማርኬቲንግ በሸሪዓ እይታ 
Gold Quest,DXN, Tiens..etc in Sharia view
(አጭር መልእክት በኢልያስ አወል)

ይህ መልእክት ከአምስት አመታት በፊት የተቀረፀ አጭር መልእክት ሲሆን በተለየያዩ መድረኮች ይህ የግብይት ሲስተም ብዙ ጎጂ ጎኖች እንዳሉት በተደጋጋሚ ቢገለፅም በዚህ ስራ ላይ የሚገኙ ሰባኪዎች ሰዎችን ጠልፈው የነሱ ሰራተኛ ለማድረግ የሚያደርጉት እልህ አስጨራሽ ጥረት ብዙዎችን እየሸነገለ ነውና ይህንን ቪዲዮ ሼር በማድረግ ከወዲሁ ሰዎችን ከጥቃት እንታደግ።


በዚህ ዙሪያ ረዘም ያለ ትምህርት ለሚፈልጉ ከታች በሚገኘው ሊንክ በቅርቡ የተለቀቀውን ረጅም ማብራሪያ ዳውንሎድ ማድረግ ይችላሉ።

⇊ ⇊ ⇊ ⇊
ኔትዎርክ ማርኬቲንግ በሸሪዓ እይታ (New Audio) 
በኢኮኖሚክስ ምሁሩ ወንድማችን ኢልያስ አወል የተሰጠ ሞያዊና ሸሪዓዊ ትንተና

Download link 

ኔትዎርክ ማርኬቲንግ... 
ጎልድ ኩዌስት... ቲያንሽ እና ሌሎችም ፒራሚዳዊ ይዘት ያላቸው የግብይት ዘዴዎችነ የሚጠቀሙ ድርጅቶችን ትክክለኛ አሰራር እና ኢስላማዊ ብያኔያቸውን ያብራራል።

- ኢስላማዊ የግብይት ደንቦችና ስርዓቶች ባጭሩ 
- የፒራሚድዊ ኔትዎርክ አስራር ምን ይመስላል?
- የኢኮኖሚ ጠበብቶችና አለም አቀፍ ተቋማት እንዴት ያዩታል?
- የኢስላም ሊቃውንት አቋም ምን ይመስላል?

ሌላም ብዙ ይማሩበታል...

ላይክና ሼር በማድረግ ወገንን እናድን!

ከዚህ አይንቱ ኔትወርክ ሰለባዎች ተሞክሮዎችን በኮሜንቶችን እንጠብቃለን

Pyramid network marketing schemes like Gold Quest,DXN, Tiens..etc
in Sharia view

by Ilyas Awol


https://www.facebook.com/tenbihat/videos/845476205549924/?fallback=1