Friday, December 5, 2014

📌 የሰጋጅ መከለያ (ሱትራ)📌




📌 የሰጋጅ መከለያ (ሱትራ)📌

የሶላት መከለያ ሰጋጅ በራሱና ከፊቱ አቋርጦ በሚያልፍ ሰው መካከል
የሚያደርገው መከለያ ነገር ነው፡፡

√ የሰጋጅ መከለያ ሱትራ የተደነገገ ስለመሆኑ

በጉዞ ላይም ሆነ ከጉዞ ውጭ፣በግዴታም ሆነ በሱንና ሶላት፣በመስጊድም ሆነ በሌላ ቦታ የሰጋጅ መከለያን (ሱትራ) ማድረግ የተደነገገ ነው፡፡

📋 ነቢዩ ﷺ :- ‹‹አንዳችሁ በሚሰግድበት ጊዜ ወደ መከለያ (ሱትራ) ይስገድ፤ወደ መከለያውም ቀረብ ይበል፡፡›› ብለዋልና፡፡
(በአቡ ዳዉድ የተዘገበ)

📋 አል ኢማም አህመድ በዘገቡት ሀዲስ ወህብ (ረዐ) ፡- ‹‹ነቢዩ ﷺ ሚና ላይ ሲያሰግዱን አንካሴ ከፊትለፊታቸው ተከሉና ሁለት ረክዓ መርተው አሰገዱን፡፡» ብለዋል።

√ የሰጋጅ መከለያን የሚመለከት ብያኔ

መከለያ (ሱትራ) ማድረግ ለሰጋጅ ዋጅብ ነው፡፡ ነቢዩ ﷺ ኢማምም ሆነ ለብቻው የሚሰግድ ሰው መከለያ ነገር ከፊት ለፊቱ እንዲደርግ አዘው አበረታተዋል፡፡ በመሆኑም አንድ ሙስሊም በሚሰግድበት ጊዜ ከፊትለፊቱ መከለያ ነገር አድርጎ በርሱና በመከለያው መካከል ሰው አቋርጦ እንዳያልፍ መከልከል ይገበዋል፡፡

📋 ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦ «ወደ ሱትራ እንጂ አትስገድ፤ ከፊትለፊትህ እንዲያልፍ ለማንም አትፍቀድ፤ እምቢ ካለህ ከሱ ጋር ሸይጣን አለውና ታገለው።»
ኢብኑ ኹዘይማ ዘግበውታል አልባኒም ሰሂህ ብለውታል።

√ የሰጋጅ መከለያ ያዘለው ጥበብ

መከለያ (ሱትራ) ለሰጋጅ የተደነገገው በርካታ ጥበቦችን አካትቶ ሲሆን ከዚህ ውስጥ፡-

1- ትኩረቱንና ተመስጦውን የሚሻማ በመሆኑ በሚሰግድ ፊት ማቋረጥን ለመከልከል፡፡

2- ሰጋጁ ሙሉ ሃሳቡንና ትኩረቱን በሶላቱ ላይ እንዲያደርግና በሌላ ጣልቃ ገብ እንዳይወሰወስ ለማድረግ፡፡

3- በሴት በውሻ ወይም በአህያ አቋርጦ ማለፍ ሶላት እንዳይቋረጥ ጥንቃቄ ለማድረግ፡፡

📋 ከአቡ ዘር (ረዐ) በተላለፈው መሰረት የአላህ መልእክተኛ ﷺ ፡- ‹‹አንዳችሁ ለመስገድ በሚነሳበት ጊዜ፤ የኮርቻ የኋላ መደገፊያ ያህል ነገር ከፊትለፊቱ ካለ መከለያ ይሆነዋል፤ የኮርቻ የኋላ መደገፊያ ያህል ነገር ከፊትለፊቱ ከሌለ ግን ሶላቱን አህያ፣ሴትና ጥቁር ውሻ ያቋርጥበታል፡፡›› አሉ ሲሉኝ፣ አቡ ዘር ሆይ! ጥቁር ዉሻን ከቀይ ወይም ከብጫ ዉሻ ምን ለየው? አልኳቸውና የወንድሜ ልጅ! አንተ አንደጠየከኝ ሁሉ እኔም የአላህ መልእክተኛን ﷺ ጠይቄ ፡-‹‹ጥቁር ዉሻ ሰይጣን ነው፡፡›› አሉ ብለውኛል፡፡ 
(ሙስሊም ዘግበውታል)

√ ሱትራን ከሚመለከቱ ድንጋጌዎች በከፊል

1- መከለያ ማድረግ ለኢማም ወይም ለብቻው ለሚሰግድም ይሆናል፡፡ ተከትሎ ለሚሰግድ ሰው ኢማሙ ለርሱ መከለያው ነው፡፡

📋 ኢብን ዐባስ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ፡- ‹‹የአላህ መልእክተኛ ﷺ በሚና ሰዎችን በማሰገድ ላይ እያሉ፣ ያኔ ለአቅመ አዳም የደረስኩ ነበርኩ፤ አንድ እንስት አህያ ላይ የተቀመጠ ሰው አግኝቼ በአንዳንዶቹ የሶላት ሰፎች ፊት ለፊት አቋርጬ አለፍኩና ከአህያዪቱ ወርጄ እንድ ግጥ ለቀቅኳት፤ ከዚያ ወደ ሶላት ሰፉ ገባሁ፤ ማንም ሰውም ድርጊቴን አልተቃወመም፡፡›› ብለዋል፡፡

ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል።
ኢማሙ ነወዊ፤ ይህ ሀዲስ የኢማሙ ሱትራ የሰገሰጆች ሱትራ መሆን እንደሚችል ያሳያል ብለዋል።

የኢማሙ ሱትራ የሰገሰጆችም ሱትራ ስለሆነ በመካከል ሰው ማለፉ ሳይሆን የሚከለከለው በኢማሙ ፊት ማለፉ ነው።

ኢብኑ አብድልበር አልኢስቲዝካር በሚለው መፅሀፋቸው ላይ ይህንን ሲያስረዱ፤ የኢማሙ ሱትራ የሰገሰጆችም ሱትራ እንደሆነ ከሚያስረዱት መካከል ሂሻም ኢብንል ጋዚ ከናፍእ ናፍእ ደግሞ ከኢብኑ ኡመር የዘገቡት ሀዲስ ነው።

ኢብኑ ኡመር እንዲህ ብለዋል፤ 
የአላህ መልእክተኛ ዙህርን ወይም አስርን እያሰገዱ ሳለ እንስሳ ከፊታቸው ልታልፍ ስትሞክር ሊመልሷት ሞከሩ፤ ማለፊያውን ሲያጠቡባትም ትኬሻቸው ግድግዳውን እንደነካ አይቻለው። ከዛም ከበስተጀርባቸው አለፈች።»

ይህም ከበስተጀርባ ስላለፈች ነው።

«የኢማሙ ሱትራ የተከታዮች ሱትራ ነው» የሚለውንም ከኢብኑ ኡመር አብዱረዛቅ ዘንድ ተዘግቧል።

2- በሰጋጅ ሰው ፊት አቋርጦ ማለፍ አይፈቀድም፡፡ ያለፈ ሰው ሀጢያተኛ ይሆናል፡፡

📋 ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል ፡- ‹‹በሚሰግድ ሰው ፊት አቋርጦ የሚያልፍ ሰው ምን (ያህል ከባድ ኃጢአት) እንዳለበት ቢያውቅ ኖሮ አቋርጦት ከሚያልፍ አርባ መቆም የተሻለ በሆነለት ነበር፡፡›› አቡ ነድር - ዘጋቢው - አርባ ቀን ወር ወይም ዓመት ይበሉ አላውቅም ብለዋል፡፡
በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ

አቋርጦ ማለፉ ከመከለያ ወዲያ ወይም ሰጋጁ መከለያ ካላደረገ ከሱጁዱ ቦታ ራቅ ብሎ ከሆነ ግን ይፈቀዳል፡፡

3- ሰጋጁ አቋርጦት የሚያልፈውን ሰው መከልከል አለበት፡፡

📋 አቡ ሰዒድ አልኹድሪ (ረዐ)
ነቢዩﷺ ፡- ‹‹አንዳችሁ ከሰዎች የሚከልለውን ነገር ከፊቱ አድርጎ ከሰገደና ሌላ ሰው ከፊትለፊቱ አቋርጦ ማለፍ ቢፈልግ ይገፍትረው፣እምቢ ካለም ይፋለመው፤ሰይጣን እንጂ ሌላ አይደለምና፡፡›› ሲሉ ሰምቻለሁ ብለዋል፡፡ ይህንንም በቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል።

4- ከእውቀት ባለቤት ዑለማእ መካከል ከፊሎቹ፤ «አስቸጋሪ ሁኔታን ማስወገድ» ከሚል አጠቃላይ መርሕ መሰረት በመካው የተከበረ መስጊድ ሰጋጅ ፊት ማቋረጥን ፈቅደዋል፡፡ ይህም በተከበረው መስጊድ ውስጥ ሰጋጅ ፊት አቋርጦ ማለፍን መከልከል በአብዛኛው ከባድ ችግር የሚፈጥር በመሆኑ ነው፡፡

5- ወደ ግድግዳ ወይም ከመስጊድ ምሶሶዎች መካከል ወይም ከመደርደሪያዎች ወደ አንዱ በመጠጋት ወይም እንደ ዱላ ያለ ነገር በማኖር መከለያ ማድረግ ይቻላል፡፡

6- በሰጋጁና በመከለያው መካከል ያለው ርቀት በአንድ ፍየል መተላፊያ በሚበቃ ያህል ይሰላል፡፡

📋 ሰህል እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በአላህ መልእክተኛ ﷺ መስገጃና በግድግዳው መካከል የፍል መተላለፊያ ያህል ርቀት ነበር፡፡›› 
በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ

ማሳሰቢያ፦ 
የሴት ሶላትን መቁረጥ ከላይ በሰፈረውና ‹‹ሶላቱን...ያቋርጥበታል›› በሚለው ሐዲስ ውስጥ ሴትን ከአህያና ከጥቁር ዉሻ ጋር የሚያነጻጽር ነገር የለበትም፡፡ 
የሦስቱ በአንድ ዐረፍተ ነገር አገባብ ውስጥ መገኘት፣ የሦስቱ ማለፍ ሶላት እንዲቋረጥ የሚያደርግበት ምክንያት አንድ ዓይነት ነው ማለት አይደለም፡፡
ማለትም ጥቁር ዉሻ ሶላት የሚቆርጥበት ምክንያት በአህያ ወይም በሴት ሁኔታ ሶላቱ ከሚቋረጥበት ምክንያት ጋር አንድ ነው ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህም በሐዲሱ ውስጥ እንደ ተጠቀሰው ጥቁር ዉሻ ሰይጣን መሆኑ አህያ ወይም ሴት ሰይጣን ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ሦስቱ በአንድ አገባብ ቢቀርቡም የተለያየ ምክንያት አላቸው፡፡ የዉሻው ምክያት ከተቀሩት ሁለቱ ተለይቶ በሐዲሱ የተጠቀሰ መሆኑ የተለያዩ መሆናቸውን እንጂ ተመሳሳይ መሆናቸውን አያመለክትም።

የሴቷ ሶላት መቁረጥ ከሰጋጁ ቀረብ ብላ አጠገቡ ማለፏ የወንዱን ስሜት ሊቀሰቅስና በሶላቱ ላይ ያለውን ተመስጦና ትኩረቱን ሊበታትንበት ይችል ይሆናል፡፡ ስለዚህም ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ ከሌላው ወንድ ተላላፊ ይበልጥ ሴት ተላላፊ ትኩረቱን ትስባለች፡፡ ለዚህ ነው -ይበልጥ የሚያውቀው አላህ ነው - በሸሪዓው የሶላትን ተመስጦና ኹሹዕ ለመጠበቅ ሲባል የሴት ልጅን በሰጋጅ ፊት ማለፍ ሶላትን ከሚቆርጡት አንዱ ያደረጋት፡፡

🔚 አይሰስቱ...
ቢያንስ ለ3 ሰው ሼር ያድርጉ!

Source: amharicfiqh.com ከማስተካከያና ጭማሪዎች ጋር የቀረበ።

📹 የሰጋጅ መከለያ (ሱትራ) 

ዓላማችን ኢስላማዊ እውቀትን ማዳረስ ነው::


SHARE